የኦሮሚያ ሴት አመራሮች ፎረም በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ሴት አመራሮች ፎረም “የሴቶች አመራር ሰጪነት ለጋራ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል በአዳማ ከተማ አባገዳ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በፎረሙ ላይ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን፣በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም ደበበ እና ከክልሉና ከፌዴራል ተቋማት የተውጣጡ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
ፎረሙ የሴቶችን የአመራር ሰጪነት አቅም በማጎልበት በቀጣይ በሀገር ግንባታ የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በተለይ ሴቶች ባለፉት አምስት የለውጡ ዓመታት የሀገርን ሰላምን ለማጽናት፣ ልማትና እድገትን ለማፋጠን ሲጫወቱ የነበሩትን ሚና ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል የብልጽግና ጉዞ እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻልን ታሳቢ ማድረጉ ተነግሯል።
በውይይቱ ሴቶች ተተኪ አመራሮችን በማፍራት ረገድ ያላቸውን ድርሻ ማሳደግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።