ካናዳ በአፍሪካ ለልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ 140 ሚሊየን የዶላር ይፋ አደረገች
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ካናዳ በአፍሪካ ለልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል 140 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ይፋ አደረገች።
የካናዳ ዓለም አቀፍ ልማት እና በፓሲፊክ ሀገራት የካናዳ ኢኮኖሚ ልማት ኤጀንሲ ተጠሪ ሚኒስትር ሃርጂት ሳጃን ኢትዮጵያን ጨምሮ በቻድ እና ግብጽ የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
ይፋ ከተደረገው ገንዘብ በተጨማሪም ለሳህል ቀጠና እና ለቻድ ሐይቅ አካባቢ ሀገራት ሰብአዊ ድጋፍ የሚውል 39 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር መመደቡን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ባለው የሰላም መሻሻል፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና እየተተገበሩ ባሉ የማገገሚያ ስልቶች ዙሪያ መምከራቸውን የካናዳ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መረጃ ያመላክታል።
ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ባደረጉት ውይይትም፥ በኢትዮጵያ እና ካናዳ መካከል ያለውን የልማት ትብብር ማሳደግ በሚቻልበት አግባብ ላይ ተወያይተዋል።
ከዚህ ባለፈም ፍትሃዊና አካታች የሆነ እርዳታ ማድረስ በሚቻልበት አግባብ እንዲሁም በሱዳን ጉዳይ ላይ ከሱዳናውያን ጋር መነጋገር በሚቻልበት አግባብ ላይም መክረዋል።
ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋ ጋር ተገናኝተው ካናዳ ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር በምትሰራቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
በተጨማሪም ሚኒስትሩ በግብጽ በተካሄደው የአፍሪካ ልማት ባንክ አመታዊ ስብሰባ ላይ ተካፍለዋል።
በአፍሪካ በነበራቸው ቆይታም ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ዓለም ቀአፍ ድርጅት ተወካዮች ጋር የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እና ግጭትና ቀጣናዊ አለመረጋጋት በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ላይ ያለውን ተፅዕኖ በተመለከተ አብራርተዋል።
በዚህ ወቅትም እንደ የዓየር ንብረት ለውጥ ያሉ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመቋቋምና የልማት ውጥኖችን እውን ለማድረግ አጋርነት እና ሁሉን አቀፍ አካታች ውይይት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።