ማህበሩ በኦሮሚያ ክልል ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በኦሮሚያ ክልል አምስት ዞኖች በፀጥታ ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን አስጀምሯል፡፡
ፕሮጀክቱ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤይድ) በተገኘ የ117 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንደሚከናወንም ተገልጿል፡፡በዚህ ፕሮጀክት 1 ሺህ 865 ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች በአንድ አመት ውስጥ እንደሚገነቡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ምክትል ዋና ፀሀፊ አቶ አበራ ሉሌሳ ተናግረዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው የውሀ ፕሮጀክቶች እንደሚጠገኑ እና ፕሮጀክቱም በምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ በደሌ፣ ኢሉባቡር እና ጉጂ ዞኖች ላይ በ11 ወረዳዎች እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
ማህበሩ ከዚህ ቀደም ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ጋር በመተባበር በደቡብ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች የቤት ግንባታ እና የተጎዱ የውሀ ፕሮጀክቶችን መልሶ የመገንባት ተግባር ሲያከናውን እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
በፍቅርተ ከበደ