Fana: At a Speed of Life!

የተከሰቱ ግጭቶች ዜጎች በህይወት እና ንብረታቸው ላይ መተማመን እንዲያጡ አድርጓል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የተከሰቱ ግጭቶች እና አለመረጋጋት ዜጎች በህይወት እና ንብረታቸው ላይ መተማመን እንዲያጡ ማድረጉን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የተከሰተው አለመረጋጋት በሰው ህይወት፣ በአምራች ተቋማት፣ በግል እና መንግስት ሃብቶች ላይ ያስከተለው ውድመትና ቀውስ የተመለከተ ጥናት የተካሄደ ሲሆን የጥናቱ ዋና ዋና ግኝቶችም ቀርበዋል፡፡

ጥናቱን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ጥናት ማዕከል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በትብብር እንዳጠኑት ተገልጿል፡፡

በኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከደቡብ፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ከሐረሪና ከሶማሌ ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያ ከሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖችና ድሬዳዋ አስተዳደር የተመረጡ 65 ወካይ ወረዳዎችና ከተሞችን ያካተተ ጥናት እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

ጥናቱ በአካባቢዎቹ በአካል በመገኘት እና ቀጥታ ተጎጂዎችን በአካል በማነጋገር እና በተዘዋዋሪ ከተጎዱት የአካባቢው አስተዳደሮች እና ከፖሊስም መረጃን በመሰብሰብ የተከናወነ ነው ተብሏል፡፡

በዚህም ከፈረንጆቹ 2019 እስከ 2020 በተጠቀሱት አካባቢዎች እና አዋሳኝ ቦታዎች የተከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋት ምክንያት ተብለው የተለዩ እና የጥፋት ተዋንያኖች ፍላጎትና አባባሽ የተባሉ ጉዳዮችና አካላት ተለይተዋል።

የግጭቶቹ ማንነትን መሰረት ያደረጉ፣ የክልልና ሌሎች የድንበር ጥያቄዎች አልተመለሱም በሚል የተፈጸሙ፣ የፖለቲካ ጥቅምን በግጭት ለማስጠበቅ የሚሉት ከብዙ በጥቂቱ በጥናቱ ከተለዩት ናቸው።

ለችግሮቹ መባባስና ተከታታይ ጉዳት ጥፋቶች በተቀናጀ ሁኔታ መካሄዳቸው፣ በአካባቢዎቹ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጥፋቱን በተገቢው ልክና ፍጥነት ማስቆም አለመቻላቸው፣ የጥፋት ሃይሎች ከፍተኛ በጀት የሚመደብላቸው እና አባባሽ ሚዲያ የሚሉት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም መንግስት ተጎጂዎችን በፍጥነት አለመደገፉ በኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጥፋት እንዳባባሰው በጥናቱ ተጠቅሷል።

ግጭቱና አለመረጋጋቱ በህይወት፣ በንብረት፣ በማህበረሰብ፣ በድርጅቶችና በመንግስት ላይ ያስከተለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከግንዛቤ ያስገባ ምላሽ በዋናነት ከመንግስት ከዚያም ከማህበረሰብ ይጠበቃል ሲልም የጥናት ቡድኑ አመላክቷል፡፡

የጥናቱ አላማ የችግሩን ምንጭ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመለየት ለቀጣይ ዘላቂና የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመፍጠር የሚያግዝ የመፍትሔ ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ እንደሆነም ነው የተነሳው፡፡

በፍሬህይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.