Fana: At a Speed of Life!

ፌዴራል ፖሊስ በ676 ሚሊየን ብር ወጪ ለሚያስገነባው የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ካምፕ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ከ676 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለሚያስገነባው የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ቢሮና ካምፕ ግንባታ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል፡፡

የመሠረት ድንጋዩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር አስቀምጠዋል፡፡

አቶ ከድር ጁሃር ÷ፌዴራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሸ ካምፕ በምስራቅ ኢትዮጵያ መቋቋሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልፀዋል።

የኢኮኖሚ ኮሪደሩ እንዳይሳካ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን እንቅልፍ የሚያሳጣና ለድሬዳዋ ፖሊስ አቅም የሚፈጥር ስለሆነ ተቋሙ ፕሮጀክቱን በከተማዋ ላይ ለማስገንባት ላሳየው ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ ያለምንም የፀጥታ ችግር በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሌት ተቀን አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ እገዛይደረጋም ብለዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ  በበኩላቸው÷ፕሮጀክቱ በምስራቅ ኢትዮጵያ የፈጥኖ ደራሽ ማዕከል ሆኖ በአካባቢው ያሉ ክፍለ ጦሮችን በአንድ ላይ ይዞ ማስተዳደር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በሀገር ውስጥ የሚያጋጥሙ ማናቸውም የፀጥታ ችግር በራስ አቅም በማስቀረት ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ የሚችል የፈጥኖ ደራሽ ኃይል እየተገነባ ነው ማለታቸውንም የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.