የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ 7 ፕሮጀክቶች ይፋ ሆኑ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ ሠባት ለህዝብ የሚውሉ ፕሮጀክቶች ይፋ ተደረጉ፡፡
ፕሮጀክቶቹ ፥ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ የጥበብና ፈጠራ ስራዎችን ለማሳደግ፣ የጤና አገልግሎትን ለማሳለጥ፣ ተፈጥሮዓዊ ሃብትን ለመጠቀምና መሰል ማህበረሰብ ተኮር የሆኑ ናቸው ተብሏል፡፡
በባህርዳር ከተማ የሚከወኑት ፕሮጀክቶች መካከል ሦስቱን በኃላፊነት ወስደው የሚገነቡ ባለሃብትና ድርጅቶች መገኘታቸውም ነው የተነሳው፡፡
የቀሩትንም ለሌሎች በጎ ፍቃደኞች ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በአንድ ፖሊ ቴክኒክ ደረጃ የዛሬ 60 ዓመት ሲቋቋም የ8ተኛ ክፍል ተፈታኞችን በመቀበል ጀምሮ ዛሬ ላይ 15 አካዳሚክ ክፍሎች በዘጠኝ ግቢዎች መማር ማስተማሩን እያሳለጠ ነው፡፡
437 አካዳሚክ ፕሮግራሞች ያሉት ዩኒቨርሲቲዉ 75 በመቶውን በድህረ ምረቃ ትምህርት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከ200 ሺህ በላይ ምሩቃንን ማፍራት መቻሉንም የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ገልጸዋል፡፡
በሁነቱ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)፣ የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ ድረስ ሣህሉ(ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን እና ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተገኝተዋል፡፡
በኃይለኢየሱስ ስዩም