Fana: At a Speed of Life!

ከእንግዲህ ሱዳናውያን ያለ ቪዛ ወደ ግብፅ መግባት አይችሉም ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብፅ በሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ሸሽተው ወደ ሀገሯ ለሚያቀኑ ሱዳናውያን የቪዛ ሕጓን ከትናንት ጀምሮ ማጥበቋ ተገለጸ።

አዲሱን አስገዳጅ የቪዛ ፖሊሲ ያወጣችው አሜሪካ እና ሳዑዲዓረቢያ ሁለቱን ተፋላሚ ኃይሎች ማደራደራቸውን እና ድርድሩ ፍሬ አፍርቶ ተግባር ላይ መዋሉን ተከትሎ መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ፖሊሲው ማንኛውም ሱዳናዊ ድንበር ከመሻገሩ በፊት ወደ ግብፅ የመግቢያ ፈቃድ ሊያገኝ እንደሚገባ ያስገድዳል፡፡

እንደ ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ÷ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘውን አዲሱን ደንብ ያወጣው በሽሽት ሰበብ ወደ ሀገሪቷ የሚገቡ አጭበርባሪዎችን እና ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመቆጣጠር ነው፡፡

ውሳኔው ለረጅም ጊዜ በበጎ መልኩ ሲያስተናግድ የነበረውን የሕጻናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን ስደተኞች መብትም የገደበ ሆኗል፡፡

በሱዳኑ ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና በመሐመድ ሃምዳን ዳግሎ በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ከሁለት ወራት በፊት በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ከ200 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ወደ ግብፅ ተሰደዋል፡፡

ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ እስካሁን ከ1ሺህ 800 በላይ የንጹሐን ሱዳናውያን ሕይወት ማለፉና ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ የሚሆኑቱ ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት መፈናቀላቸው ተመላክቷል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.