አሜሪካ ከቻይና የገጠማትን ፉክክር ለመገዳደር “ዩኔስኮ”ን ዳግም ለመቀላቀል ጠየቀች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ከቻይና የገጠማትን የባለ ብዙ ጎራ ፉክክር ለመገዳደር የተመዱን የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል ድርጅት “ዩኔስኮ” በድጋሚ ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርባለች፡፡
አሜሪካ ድርጅቱን ከለቀቀች በኋላ የቻይና ሚና መጉላቱ እጅግ እንዳሳሰባት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን መጋቢት ወር ላይ ለኮንግረሱ ያቀረቡትን ሐሳብ አስታውሶ አር ቲ ዘግቧል፡፡
አሁን ላይ አሜሪካ “ነፃ ዓለም የመፍጠር ራዕይ” የሚለውን አዲስ መርኅ ይዛ በድርጅቱ ለማስተዋወቅ ዐቅዳለች ተብሏል፡፡
ድርጅቱን በፈቃዷ ከለቀቀች አምሥት ዓመታት በኋላ ነው ባሳለፍነው ሠኔ 8 ማመልከቻዋን በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ለ“ዩኔስኮ” ያስገባችው፡፡
አሜሪካ ከድርጅቱ ራሷን ባገለለችባቸው 5 ዓመታትያልከፈለቻቸውን ክፍያዎች ሸፍና ወደ ድርጅቱ እንድትመለስ አንቶኒ ብሊንከን ኮንግረሱን መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
ሚኒስትሩ ከድርጅቱ ወጥተው በነበረበት ጊዜም ከፍተኛ ዕዳ ሊኖርባቸው ስለሚችል ለመመለስ የሚያስችል 150 ሚሊየን ዶላር ያኅል በጀት ኮንግረሱ እንዲመድብ አሳስበው ነበር።