የ4 ሀገራት መሪዎች ከሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች መሪዎች ጋር ሊወያዩ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ እና ደቡብ ሱዳን መሪዎች ከጀነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን እና ጀነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ ጋር እንደሚወያዩ ኢጋድ አስታወቀ፡፡
የሱዳንን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ያለመው የአራትዮሽ ውይይቱ÷ በቀጣዮቹ 10 ቀናት ውስጥ በአካል እንዲካሄድ መወሰኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
ውይይቱ በሱዳን ተባብሶ የቀጠለውን ጦርነት ማስቆም፣ ሁሉም አይነት ግጭቶች እንዲቆሙ እና ወታደራዊ አመራሮቹም ጦርነቱን ለማቆም ቁርጠኛ አቋም እንዲወስዱ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ከጀነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን እና ከጀነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ ጋር የሰብአዊ እርዳታ ኮሪዶር መክፈት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ከስምምነት መደረሱን የኬንያው ፕሬዚዳንት ጠቁመዋል፡፡
የኮሪዶሩ መከፈት አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በተለይም ሴቶች፣ ሕጻናት፣ በግጭቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እና ሌሎች ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል፡፡
እንዲሁም በቀጣይ ሦስት ሳምንታት በሱዳን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ የምክክር ሂደት ለመጀመር የመሪዎች ጉባዔው ከስምምነት ላይ መድረሱን ነው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ የገለጹት፡፡
የምክክሩ ዓላማም የሱዳን ሕዝብ የሚወያይበት እና መፍትሔ የሚያበጅበት እድል መፍጠር ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከዚህ ቀደም ኢጋድ በሱዳን ያለውን አለመረጋጋት ለመፍታት ሶማሊያ፣ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ያሉበት የሶስትዮሽ ስብስብ መመስረቱን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ሩቶ በአሁኑ ስብስብ ውስጥ ኢትዮጵያ መካተቷን ገልጸዋል፡፡
ኬንያ በሊቀ-መንበርነት የምትመራው የአራትዮሽ ስብስብ(ኳርቴት) በሱዳን ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡