በአማራ ክልል ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ ማስጀመሪያ መርሐግብር እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 6 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ
ሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ ዐሻራ የአማራ ክልል ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በባሕር ዳር እየተከናወነ ነው።
” ነገን ዛሬ እንትከል ” በሚል ሀሰብ ሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ በሀገር አቀፍ ደረጃ መጀመሩ ይታወሳል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ/ር) በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኖች ተዘጋጅተው 6 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን ገልፀዋል።
ይህም በክልሉ የነበረውን 14 በመቶ የደን ሽፋን ወደ 16 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተተከለው ችግኝ 700 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን መሆኑንም ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡
ከተተከሉት ችግኞች መካከል 25 በመቶ የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዙር የችግኝ ተከላ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የገለጹት ኃላፊው ÷ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ችግኞች እንደሚተከሉ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።