Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ አመታት የነዳጅ ዘይት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ አመታት ዓለም ላይ የነዳጅ ዘይት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ዓለም አቀፉ የኃይል ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ባወጣው የ2023 አጋማሽ አመት የገበያ ሪፖርት ላይ ከሚከሰተው ከፍተኛ የነዳጅ ፍላጎት አንጻር በቀጣዮቹ አመታት ምናልባትም የአቅርቦት እጥረት ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቋል።

እንደ ኤጀንሲው ገለጻ በተጋመሰው የፈረንጆቹ 2023 ዓለም ላይ የነዳጅ ዘይት ፍላጎት በቀን 102 ነጥብ 3 ሚሊየን በርሜል መድረሱን አመላክቷል።

ይህም ከእስከዛሬዎቹ ከፍተኛው መሆኑን ያነሳው የኤጀንሲው ሪፖርት፥ እስከ ፈረንጆቹ 2028 ድረስ የቀን የነዳጅ ዘይት ፍላጎት አሁን ካለው በ6 በመቶ እንደሚጨምርም ነው ያመላከተው።

ለዚህ የነዳጅ አቅርቦት ፍላጎት መናር አዳጊ ሀገራት የሚያስመዘግቡት ፈጣን እድገት ምክንያት እንደሚሆንም ነው ኤጀንሲው የሚገልጸው።

በተጨማሪም በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች እና በአቪየሽን ኢንዱስትሪው የሚኖረው የነዳጅ አቅርቦት ፍላጎት ሌላኛው ምክንያት መሆኑንም ገልጿል።

ከሚኖረው የአቅርቦት ፍላጎት ውስጥም የእስያ ሀገራት 75 በመቶውን ድርሻ እንደሚይዙም ነው ሪፖርቱ የሚያመላክተው።

በአንጻሩ አውሮፓ እና አሜሪካ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለኃይል አቅርቦት የሚያወጡትን ወጪ በመቀነስ አማራጭ መንገዶችን እንደሚከተሉም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በተያዘው የፈረንጅቹ አመት ለነዳጅ ዘይት ከፍተኛ ወጪ አውጥታለች የተባለችው ቻይና ከቀጣዩ የፈረንጆቹ አመት ጀምሮ የነዳጅ ዘይት ፍላጎቷ በእጅጉ ይቀንሳል ነው የተባለው።

እንደ ኤጀንሲው ሪፖርት ቤንዚን፣ ኢቴን እና ናፍታ በስድስቱ አመታት ውስጥ ከኮቪድ ወረርሽኝ በፊት ከነበረው አንጻር እስከ 90 በመቶ የአቅርቦት ፍላጎት ጭማሪ የሚታይባቸው ናቸው።

አሁን የሚታየው የነዳጅ ዘይት አቅርቦት ግን ከፈረንጆቹ 2028 በኋላ ከፍተኛ ቅናሽ ያሳያል ማለቱን የዘገበው አር ቲ ነው።

በፈረንጆቹ 2028 የቀን የነዳጅ ዘይት የፍጆታ ፍላጎት ወደ 0 ነጥብ 4 ሚሊየን በርሜል ይወርዳል ያለው የኤጀንሲው ትንበያ፥ ይህም ዝቅተኛ የካርበን ልቀትን ለማሳካት ለተያዘው እቅድ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ጠቅሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.