Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ሁለት ዞኖች ጤፍን በኩታ ገጠም ለማልማት እየሰሩ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ እና ማዕከላዊ ዞኖች አርሶ አደሮች ጤፍን በኩታ ገጠም የማልማት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኝ የክልሉ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ማዕከል አስታወቀ።

በማዕከሉ የጤፍ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ኃይሉ እንዳሉት÷ በሁለቱም ዞኖች 50 ሺህ አርሶ አደሮችን ወደ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ለማሸጋገር በ850 የጤፍ ክላስተር ተደራጅተው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው።

አርሶ አደሮቹ ጤፍን በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ ለማልማት እስካሁን ባደረጉት እንቅስቃሴ 12 ሺህ 750 ሄክታር ማሳ በጤፍ ምርጥ ዘር እየሸፈኑ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

አርሶ አደሮቹ ግብርናን በዘመናዊ መንገድ ማከናወን እንዲችሉ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲቲዩት የበጀት ድጋፍ እንዳደረገላቸውም ነው አቶ ቴዎድሮስ የገለጹት።

በማዕከሉ በኩል በስድስት ወረዳዎች ለሚገኙ የአቅም ውስንነት ላለባቸው ሴት አርሶ አደሮች ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በትራክተር የማረስ ስራ እየተከናወነ እና ማዕከሉ የጤፍ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ ከሁለገብ የሕብረት ስራ ዩኒየኖች ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል።

አርሶ አደሮቹ በበኩላቸው÷ ግብርናን በእርሻ ትራክተር ማረስ ጊዜ፣ጉልበትና ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስቀርላቸውና በትራክተር ማረስ የአፈር ለምነት ጠብቆ በሰብል ላይ የሚከሰቱ ተባዮችን እና አረምን እንደሚቀንስ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.