Fana: At a Speed of Life!

ተተኪ ሴት አመራሮችን በስፋት በማፍራት ወደ አመራር እንዲመጡ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገርና ለህዝብ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ተተኪ ሴት አመራሮችን በስፋት በማፍራት ወደ አመራር እንዲመጡ እየተሰራ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ ።

በየደረጃው ለሚገኙ የብልፅግና ፓርቲ ተተኪ ሴት አመራሮች ላለፉት 10 ቀናት በአዳማ አባገዳ አዳራሽ ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል ።

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፥ ስልጠናው የተዘጋጀው ተተኪ ሴት አመራሮች የፓርቲውን ተልዕኮና እሴት በትክክል እንዲገነዘቡ ለማስቻል ነው።

ብልፅግና ሁሉንም ህዝቦች ያማከለ አካታች ፓርቲ ነው ያሉት አቶ አደም፥ በሴቶች ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ መርሐግብር ተቀርፆ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይ በርካታ ተተኪ ሴት አመራሮችን ማፍራት በዋናነት ጠንካራ ፓርቲ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

በቀውስ አስተዳደር ፣ ተግባቦትና ውጤታማ ስራዎች በማከናወን ረገድ ሴቶች የተሻለ ሚና እንዳላቸውም ገልጸዋል።

በተለይ ለሀገርና ለህዝብ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ተተኪ ሴት አመራሮችን በስፋት በማፍራት ወደ አመራር እንዲመጡ እየሰራን ነው ብለዋል።

ሴቶች ከኮታ አመለካከት እንዲወጡ አቅም ገንብተው በብቃታቸው የአመራር ቦታ በስፋት እንዲይዙ ለማስቻል ስልጠናው አንዱ ተግባር መሆኑንም ነው የገለጹት።

ከዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች የተላቀቀ፣ ከተናጥል እውነት ይልቅ የወል እውነት ግንባታ ላይ ያተኮረ፣ የህዝቦችን ማንነት፣ ባህል፣ ቋንቋ እንዲሁም ወንድማማችነት መሰረት ያደረገ የመግባባት ዴሞክራሲን ለመለማመድ ጭምር እንሰራለን ብለዋል አቶ አደም ፋራህ።

ስልጠናው የብልፅግና ፓርቲ የሴት አመራሮችን በማብቃትና በአዲሲቷ ህብረብሔራዊት ኢትዮጵያ ግንባታ ላይ የድርሻቸውን እንዲውጡ እንደሚያግዝ የገለጹት የፓርቲው ሴቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ዘሃራ ሁመድ ናቸው።

ተተኪ ሴት አመራሮችን በማብቃት የፖለቲካ ተሳትፎ ንቁ ሚና እንዲኖራቸው፣ በፓርቲው የቀጣይ 10 ዓመት ዕቅድ፣ በተግባቦትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ስልጠናው ላለፉት 10 ቀናት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ስልጠናውን የወሰዱ ተተኪ ሴት አመራሮች በየደረጃው በሚገኘው የአመራር ማዕቀፍ ውስጥ በመግባት በሂደት እየበቁ እንደሚሄዱ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.