መንግሥት ስለሰላም አብዝቶ የሚናገረው የሁሉም ነገራችን መሰረት በመሆኑ ነው – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት ስለሰላም አብዝቶ የሚናገረው እና በተግባርም የሙሉ ጊዜ ሥራ አድርጎ የሚሰራው ሰላም የሁሉም ነገራችን መሰረት በመሆኑ ነው ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ በሰላም ሽፋንነት መንግሥትን ማጠልሸት ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስፈንና ሰላምን ለማረጋገጥ እየወሰደ ካለው እርምጃ ጎን ለጎን ልማትን ለማፋጠንና የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ ብርቱ ጥረት አድርጓል ብለዋል። ታላሚ ውጤቱም የተሳካ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ይህንን ጥረት እና ውጤት አንዳንድ ወገኖች በማጠልሸት መንግስት ለሰላም ትኩረት እንዳልሰጠ በማስመሰል መንግስሥትን ሲያጥላሉ እያየን ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት በመሆኑና ጉዳዩ ከቅን ልቦና የሚቀርብ ከሆነ ወቀሳና ትችቱ ክፋት እንደሌለው ገልጸው÷ ነገር ግን በእንዲህ አይነት የማጠልሸት ሥራ ላይ የተጠመዱ ሰዎች አብዛኞቹ በሚረጩት የጽንፈኝነት አስተሳሳብ፣ በሃሰተኛ መረጃ ወይም ሆን ብለው የተዛቡ መረጃዎችን አጋነው በማቅረብ አንዱን አካባቢ ከሌላው፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ፣ ከዚህም ጠርቀም ያለ ትርፍ የሚያገኙ፣ ሰላም ከተረጋገጠ ጥቅማቸው የሚቋረጥባቸው እና በርግጥም ሰላም እንዳይመጣ የማይፈልጉ ናቸው ብለዋል፡፡
በጽንፈኝነትና ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ አግባብ ጥቅምና ፍላጎታቸውን ለማሳከት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን እያጀገኑ በንጹሃን ደም መፍሰስ ጥቅማቸውን የሚያረጋግጡ የደም ነገዴዎች ናቸው ብለዋል ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ጠንከር ብሎ እርምጃ መውሰድ ሲጀምር አንድን አካባቢና ሕዝብ በተለየ መልክ ለማጥቃት እንደሚንቀሳቀስ አድርገው ያቀርባሉ ነው ያሉት፡፡
እነዚህ አካላት “ጠላታችን” በሚሉት ላይ የመከለከያ ሃይላችን ርምጃ ሲወስድ ጀግናችን ይሉታል፤ ጥቅማችንን ያስከብራል የሚሉት የጥፋት ቡድን ላይ ርምጃ ሲወስድ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መከታ የሆነውን የመከለካያ ሠራዊታችንን ያንቋሽሻሉ፤ አልፎም የአንድ ቡድን ሠራዊት እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት የኅብረተሰቡን ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታትና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ የሚያደርገውን ጥረት በማቆም የጥፋት ኃይሎቹ በሚፈጥሩት አጀንዳ ላይ ብቻ የሙጥኝ እንዲል ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡
በማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እየተገኙ ያሉ ስኬቶቻችን ስለሚያስበረግጋቸው የማይገናኙ ጉዳዮችን በመቀጣጣልና የሀሰት መረጃዎችን በመርጨት ለማንኳሰስ እንደሚሞክሩም ነው የጠቆሙት፡፡
የመንግሥት አቅጣጫ በመደመር እሳቤ ሰላም፣ ልማትና አካታች ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በኅብረ-ብሔራዊነት፣ በወንድማማችናትና በእኩልነት ማዕቀፍ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
እነዚህን ጉዳዮች በተደማሪነት ያከናውናል እንጅ አንዱን በመተው ወደ ሌላው አያተኩርም ያሉት ሚኒስትሩ÷ ምክንያቱም ግቡ ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ማድረግ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡ መንገዱ ወደ ዘላቂ ሀገራዊ ብልጽግና ብቻ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
መንግሥት ስለሰላም አብዝቶ የሚናገረው፣ በተግባርም የሙሉ ጊዜ ሥራ አድርጎ የሚሰራው ሰላም የሁሉም ነገራችን መሰረት በመሆኑ ነው ያሉት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)÷ ግጭትና ጦርነት የዜጎችን ደህንትና ነፃነት አደጋ ላይ ይጥላሉ፤ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱን ያውካሉ፤ የሰው ልጆች ህይወትን ይቀጥፋል፣ ሀብትና ንብረት እንደሚያወድሙ አስገንዝበዋል፡፡
ሰላም በሌለበት ብልፅግናን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ግጭትና ጦርነት የብልፅግና ፀር ናቸው የምንለው ከዚህ በመነሳት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትሩ እንደገለጹት÷ የብልፅግና ዓላማ የሰው ልጅን የነፃነት፣ የእኩልነት እና ሁለንተናዊ ፍላጎት ማሟላት ነው፡፡
ይህንን ፍላጎት ለማሟላት በተደመረ አቅም መንቀሳቀስና መትጋት፣ በዚህም ያለምነው ግብ እንዲሳካ የሁሉንም ወገኖች ርብርብ፣ በሰላማዊ አማራጭ ብቻ ፍላጎቶችን ለማሳካት መንቀሳቀስን ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም አሁን እየተረጋገጠ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ቀጣይነቱን ለማረጋገጥና ለማጽናት የሁሉም ዜጎች፣ አከላትና መንግሥትን የጋራ ጥረት ይጠይቃልና ሁሉም የበኩሉን ለመወጣት ትጋቱን አጠናክሮ መቀጣል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
እንደመንግሥት ዘላቂ የሕዝባችንን ብልጽግና ማረጋገጥ ዋናው ዒላማችን ነው ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ብልጽግናችን የሚረጋገጠው ደግሞ የፖለቲካ ነጋዴዎች በየጊዜው በሚፈጥሩት ጥቃቅን አጀንዳ የሚደናቀፍ ሳይሆን በጠራ የልማት እና የዕድገት አቅጣጫ የሚመራ፣ ግልጽ መዳረሻ እና ርዕይ ያለው ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ይህንን ለማሳካት ከዒላማችን ላይ ዐይናችንን ሳንነቅል በትጋት እንሰራለን የሉት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ÷ ሕዝባችንም በሁሉም የልማት እና የሰላም አጀንዳዎቻችን ላይ አጋርነቱን እና ተሳትፎውን እያስቀጠለ ነው ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ነጋዴዎች እየከሰሩ ዒላማችንን እናሳካለን፤ ዐይናችን 24/7 ከዒላማችን ላይ ነው፤ በሰላም ሽፋን መንግሥትን በማጠልሸት የሚደናቀፍ ጉዞ የለንም ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡