የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በሰላማዊ ድርድር ሊያበቃ ይገባል- ሲሪል ራማፎሳ
አዲስ አበባ፣ሰኔ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ የሰላም ልዑካን ቡድን አካል በመሆን ሩሲያ የሚገኙት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ÷ ለሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬን ጦርነት መቆም እንዳለበት ተናግረዋል።
ራማፎሳ ትናንት በሴንት ፒተርስበርግ በኮንስታንቲኖቭስኪ ቤተ መንግስት ተገኝተው ÷“ይህ ጦርነት ማብቃት አለበት፤በድርድር እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፈታት አለበት” ብለዋል።
ምንም እንኳን ዩክሬን ባለፈው ሳምንት የሩሲያ ሃይሎችን ለመግፋት መልሶ ማጥቃት ብትጀምርም÷ ራማፎሳ ስምምነትን የሚሻ ተከታታይነት ያለው “ደህንነትን የማረጋገጥ እርምጃዎች” ላይ የአፍሪካ የሰላም ልዑክ ያወጣቸውን 10 ነጥቦች አቅርበዋል፡፡
ሰባት የአፍሪካ መሪዎችን ያቀፈው የሰላም ልዑካን ቡድን “የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት መቆም አለበት የሚል ግልጽ መልዕክት ይዞ ወደ ሀገራቱ ማቅናቱንም አስገንዝበዋል፡፡
ራማፎሳ÷ጦርነቱ በአፍሪካ አህጉር እና በሌሎችም በርካታ የዓለም ሀገራት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን የአፍሪካ መሪዎች የያዟቸው ብዙዎቹ ሃሳቦች የተሳሳቱ ናቸው ብለው የሚያምኑበትን ምክንያት በዝርዝር አቅርበዋል።
ዩክሬን እና ምዕራባውያን ግጭቱን የጀመሩት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ሩሲያ ጦሯን ወደ ድንበር ከመላኳ ረጅም ዓመት በፊት ነው ሲሉ አብራርተዋል
በኪየቭ የታገደውን ከዩክሬን ጋር መደራደርን በተመለከተም ሩሲያ ፈፅሞ አልቀበልም ብላ እንደማታውቅ አስረድተዋል።
ሰባት የአፍሪካ መሪዎችን ያቀፈው የሰላም ልዑካ በዩክሬኑ ከፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ጋር በኪየቭ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከሩ ይታወሳል፡፡
በዚህ ወቅትም ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ከሩሲያ ጋር የሰላም ድርድር የምናደርገው ሞስኮ ጦሯን ከዩክሬን ግዛት ካስወጣች በኋላ ነው ማለታቸውን አልጀዚራ ዘገቧል።