የድባቴ መንስኤ ፣ ምልክቶችና መከላከያ መንገዶች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድ ሰው ከገባበት ሀዘን ወይም ጥሩ ያልሆነ ስሜት በቶሎ መላቀቅ ካልቻለ የድባቴ ስሜት አጋጥሞታል ማለት ይቻላል፡፡
የድባቴ ስሜት በብዙ ሰዎች ላይ የሚከሰት ችላ ከተባለ ግን የአዕምሮ ጤናን የሚያውክ ደረጃ እንደሚደርስ የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የድባቴ ምልክቶች በሁሉም ሰው ላይ አንድ አይነት ላይሆኑ ይችላሉ፤ ደረጃ፣ ቆይታና አስከፊነት እንደየግለሰቡ የድባቴ ሁኔታ ይለያያል፡፡
ሆኖም ተከታታይ የሆነ የሃዘን፣ የንዴት፣ የብስጭት፣ የቁጣና የባዶነት ስሜት፣ የተስፋ ማጣትና ጨለምተኝነት አመለካከት፣ ራስን መውቀስ፣ ዋጋቢስና ረዳት የለሽ የመሆን ስሜት፣ በትንሽ በትልቁ መበሳጨትና ቅብጥብጥነት፣ ለወትሮው በፍቅር ለምናከናውናቸው ተግባራት ፍላጎት ማጣት፣ ድካምና ተነሳሽነት ማጣት የድባቴ ምልክቶች ናቸው፡፡
እንዲሁም አትኩሮት ማጣት፣ ዝንጉነትና ውሳኔ ለመስጠት መቸገር፣ መጫጫን፣ የእንቅልፍ መዛባት (እንቅልፍ ማጣት ወይም ለረዥም ጊዜ መተኛት)፣ ከመጠን ያለፈ መመገብ ወይም የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ራስን ማጥፋት መፈለግና መሞከር፣ በህክምና መታገስ ያልቻለ ራስ ምታት፣ ቁርጠት፣ ቁርጥማትና የምግብ አለመፈጨት ችግር ካጋጠመ ድባቴ መኖሩን ይጠቁማል፡፡
አዕምሮን የሚረብሽ ከባድ የህይወት አጋጣሚ፣ የሚወዱት ሰው በሞት መለየት፣ ከሰዎች ጋር ያለ ሠላማዊ ግንኙነት መናጋት፣ አዕምሮ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ የሆነ ሀሳብና ሁኔታ ሲገጥም፣ ጭንቀት፣ መገለልና የሞራል ውድቀት ለድባቴ ከሌላው ሰው ይልቅ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን እንደሚያመላክት የጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መረጃ ያመላክታል፡፡
ድባቴን እንዴት ማስወገድ ይቻላል?
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት መከተል፣ ከአልኮል፣ ከትምባሆ እና ከአደንዛዥ እፆች መቆጠብ፣ አሉታዊ ሀሳቦችን ከአዕምሮ አስወግዶ አዎንታዊ ጎኖችን ማሰብ መለማመድ፣ በህይወት ውስጥ ለችግሮች ፍፁም የሆነ መፍትሄ እንደሌለ ማስታወስ ናቸው፡፡
እንዲሁም የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለማለፍ በትዕግስት ጠንክሮ መስራት፣ ለሳቅ ለጨዋታ በአጠቃላይ ለመዝናኛ ጊዜ ማበጀት፣ ለሰዎች በጎ ነገር በማድረግ መልካም ወዳጅነትን ማፍራት፣ ጭንቀትና ስጋትን ለቅርብ ሰው ማካፈልን መልመድ።