ኢጋድ የምግብ ደህንነት ስትራቴጂ ወደ ስራ እንዲገባ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የምግብ ደህንነት ስትራቴጂ ወደ ስራ እንዲገባ ውሳኔ አሳልፏል።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው የኢጋድ የምግብ ደህንነት እና የድህረ ምርት ብክነት አስተዳደር ስትራቴጂዎች ላይ ያተኮረ የሚኒስትሮች ስብስባ ዛሬ በአዲስ አበባ መጀመሩ ይታወቃል።
በጉባኤው የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የኢጋድ አባል አገራት የግብርና ሚኒስትሮች፣ የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት(ፋኦ) ተወካዮች እና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ከቀትር በኋላ በነበረው የስብስባ ውሎ የኢጋድ አባል አገራት የቀጣናው የምግብ ደህንነት ስትራቴጂ ወደ ስራ እንዲገባ አጽድቀዋል።
ስትራቴጂው ለቀጣይ አምስት ዓመታት እንደሚተገበር ተገልጿል።
ኢጋድ በፋኦ ድጋፍ አማካኝነት በአገራት እና በቀጣናው የምግብ ደህንነት ስርዓትን ማጠናከር እና በምግብ ግብይት ውስጥ ፍትሐዊ አሰራሮች እንዲተገበሩ ማድረግን አላማ ያደረገ የምግብ ደህንነት ስትራቴጂ እ.አ.አ በ2022 ማዘጋጀቱ የሚታወስ ነው።
የሚኒስትሮች ስብስባው በቀጣይ የድህረ ምርት ብክነት አስተዳደር ስትራቴጂ ላይ በመምከር ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል፡፡