ከንቲባ አዳነች አቤቤ የቀዳማይ ልጅነት ልማት የንቅናቄ ሳምንትን አስጀምሩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ “ሕጻናት የነገ ተስፋ ለአዲስ አበባ” በሚል መሪ ሃሳብ የቀዳማይ ልጅነት ልማት የንቅናቄ ሳምንትን አስጀምረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ለውጥ በዘላቂነት ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና የሚኖረው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አንስተዋል፡፡
ትግበራውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል የአንድ ሳምንት ከተማ አቀፍ ንቅናቄ በዛሬው ዕለት መጀመሩንም ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
መርሐ ግብሩ ከፅንስ ጀምሮ እስከ 6 ዓመት የዕድሜ ክልል ባሉ ጨቅላ ሕፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“በዚህ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም እንደ ሀገር በትውልድ መካካል ያጋጠመን ስብራት ክምንጩ ለመፈወስ በዚህ የዕድሜ ክልል ላይ አበክረን መስራት እንዳለብን ተረድተናል” ነው ያሉት።
የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርትን ለማሸጋገር የሚያስችል በጥናት እና ምርምር ላይ የተደገፈ ስራ ለመስራት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙንም ጠቁመዋል፡፡
የቀዳማይ ልጅነት ልማት እና እንክብካቤ የሚካሄድበት የዕድሜ ክልል ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው ነገር ግን በሰው ልጅ ሕይወት ወሳኙ የሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት የሚጣልበት የዕድሜ ክልል መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ከተማ አስተዳደርም ለዚህ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ “ሕጻናት – የነገ የአዲስ አበባ ተስፋ’’ የሚል ፕሮግራም ተቀርጾ ወደ ትግበራ መገባቱንም ነው የገለጹት።