Fana: At a Speed of Life!

ሕገ-ወጥ የማዕድን አምራቾችን ስርዓት ለማስያዝ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል – አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ሕገ-ወጥ የማዕድን አዘዋዋሪዎችን እና አምራቾችን ስርዓት ለማስያዝ የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማዕድን ቁጥጥር ኮማንድ ፖስት ባለፉት ሶስት ወራት የተከናወኑ ሥራዎችን በዘርፉ የተሠማሩ ባለሃብቶች በተገኙበት ገምግሟል፡፡

በመድረኩ አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ በመከላከያ ሠራዊት የ404ኛ ኮር አዛዥ ጄነራል ሰይፈ አንጌን ጨምሮ የጸጥታ እና የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን÷ በማዕድን ዘርፉ ላይ የሚስተዋለው ህገ-ወጥ ተግባር ሀገርን ወደ ኢኮኖሚ ስብራት ለማስገባት ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ባለሃብቱ ከተሰማራበት ዘርፍ ራሱን ጠቅሞ ሀገሩንና የአካባቢውንም ማኅበረሰብ እንዲጠቅም ይፈለጋል ያሉት ርዕሰ-መስተዳድሩ÷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዘርፉ የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ ምርትና ዝውውር ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፥ ከቁጥጥሩ በኋላ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ ምርት መሻሻል አሳይቷል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይም መንግስት ሕገ-ወጥ የማዕድን ምርት አዘዋዋሪዎችንና አምራቾችን ስርዓት ለማስያዝ የጀመረውን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡

ጄኔራል አበባው ታደሰ በበኩላቸው÷ከማዕድን ማምረት በስተጀርባ ዓላማ በመያዝ የአካባቢው ሕዝብ እና ሀገር እንዳትጠቀም በሚሠሩ ሕገ-ወጥ አካላት ላይ ፈቃዳቸውን ከመሠረዝ ጀምሮ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ የተሠማሩ እውነተኛ ባለሃብቶችን ማበረታታት፣ መደገፍና ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

መንግስት ሀገራቸውን ጠቅመው፣ ራሳቸውን ለመጥቀም የሚሠሩ ባለሃብቶችን ለመደገፍ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ የተሠማሩ ባለሃብቶች በበኩላቸው፣ የችግሩ መፍትሔ ቁጥጥሩን ማጠናከር መሆኑን ጠቁመው÷ መንግስት የጀመረውን ህጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.