በኢትዮጵያ በሣምንት ከ70 እስከ 80 ሺህ ዜጎች በወባ በሽታ እየተጠቁ መሆኑ ተመለከተ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በሣምንት ከ70 እስከ 80 ሺህ ዜጎች በወባ በሽታ እየተጠቁ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቻምየለሽ ሲሳይ እንደገለጹት÷ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሣምንት ከ70 እስከ 80 ሺህ ሰዎች በበሽታው እየተጠቁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ውጭ በሁሉም ክልሎች በሽታው መኖሩን ባለሙያዋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ እና በሽታውን ለመከለከል የሚሰራጩ ግብዓቶችን በአግባቡ አለመጠቀም ችግሩ እንዲስፋፋ ስለማድረጉም ጠቁመዋል፡፡
በሽታውን ለመከላከልም በዚህ ዓመት 19 ነጥብ 7 ሚሊየን አጎበር መሰራጨቱን ጠቁመው÷ ከዚህ በፊት የተሰራጩቱን ጨምሮ በሕብረተሰቡ ዘንድ 30 ሚሊየን አጎበር አለ ብለዋል፡፡
በሚቀጥለው ዓመት አጎበርን ከወሰዱ ከ3 ዓመት በላይ ለሆናቸው አካባቢዎች ስርጭት እንደሚደረግ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ ዓመት በድንገተኛ አደጋዎች እና በተለያዩ ምክንያቶች አጎበራቸውን ላጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ስርጭት እንደሚኖር አመላክተዋል፡፡
እንዲሁም በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ በሚስፋፋባቸው አካባቢዎች ከፊታችን ሐምሌ እስከ መስከረም ድረስ በ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶች ላይ የኬሚካል ርጭት እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡
እንደ ሀገር የወባ መድሃኒት እጥረት እንዳለ ተደርጎ የሚወራው ሐሰት ስለመሆኑም ጠቁመው÷ የመድኒት ዕጥረት አለብን የሚሉ ክልሎች ለጤና ሚኒስቴር ጥያቄያቸውን በማቅረብ መድሃኒት ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ