Fana: At a Speed of Life!

የሽብር ወንጀል ቀስቃሽ መልዕክቶች አስተላልፏል ተብሎ በተጠረጠረው ግለሰብ ላይ የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፖሊስ በማኅበራዊ ሚዲያ የሽብር ወንጀል ቀስቃሽ መልዕክቶችን አስተላልፏል ብሎ በጠረጠረው ግለሰብ ላይ ፍርድ ቤቱ የዘጠኝ ቀናት የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜ ፈቀደ።

የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜውን ለፖሊስ የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አሳዬ ደርቤ በተባለው ተጠርጣሪ ላይ የዘጠኝ ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜ የፈቀደው÷ ከዚህ በፊት በሰጠው የ14 ቀናት ጊዜ ውስጥ በፖሊስ የተሠሩ ሥራዎችን እና በተጠርጣሪ ጠበቆች የተነሱ የመከራከሪያ ነጥቦችን ተመልክቶ ነው ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ÷ አሳዬ ደርቤ የተባለው ግለሰብ በተጠረጠረበት የሽብር ወንጀል ከዚህ በፊት በተሰጠው የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ውስጥ የሰራቸውን የምርመራ ስራዎችንና ቀሪ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያቶቹን ዘርዝሮ ለችሎቱ አቅርቧል።

በዚህም የግለሰቡን የጣት ዐሻራና ፎቶ የማስነሳት ሥራ መሥራቱን፣ ቃል የመቀበል ሥራ መከናወኑን፣ የባንክ የገንዘብ ዝውውር የማጣራት ሥራ መሠራቱን እና የፎረንሲክ ማስረጃ መሰብሰቡን ገልጿል።

ቀረኝ ካላቸው የምርመራ ሥራዎች ማለትም ምስክር ቃል መቀበል ፣ የተሰበሰቡ የፎረንሲክ ማስረጃ ማስተንተን፣ ግብረአበር ተከታትሎ የመያዝ ሥራዎች የሚሉትን ነጥቦችን ጠቅሶ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው÷ ተጠርጣሪው ላይ ፖሊስ ያቀረበው ጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያቶች ተጠርጣሪውን አስሮ ለማቆየት ሕጋዊ መሠረት የለውም ሲሉ ተከራክረዋል።

ፖሊስ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ምስክር ስለመቀበሉ ባልገለፀበት ሁኔታ ላይ ምስክር ለመቀበል ብሎ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቁ አግባብነት የለውም የሚሉ የመከራከሪያ ነጥቦችንም አንስተዋል።

ደንበኛቸው በሙያው በማኅበራዊ ሚዲያ አስተላልፏል የተባለው መልዕክት በሽብር ወንጀል የሚያስጠይቀው ተግባር አይደለም በማለትም ጠበቆቹ ተከራክረዋል።

በመሆኑም ደንበኛቸው በዋስ ቢወጣ የሚያጠፋው ማስረጃ አለመኖሩን እና ሕግን አክብሮ የሚቀርብ መሆኑን የጠቀሱት ጠበቆቹ÷ የደንበኛቸው ባለቤት ለመውለድ መዳረሷን ጠቅሰው ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱን እንዲያከብርለት ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪው በሙያው ባስተላለፈው መልዕክት ምክንያት ነው የታሰረው ለሚለው የጠበቆች መከራከሪያ ነጥብን በሚመለከት በሙያው እንዳልታሰረ ገልጿል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ያልፈጸመውን ድርጊት የግድያ ተግባር ፈፅመዋል በማለት የተዛባ መረጃ በማሰራጨት፣ ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ለሽብር ተግባር የሚያነሳሱ ግጭት ቀስቃሽ መልክቶችን ለተከታዮቹ ሲያስተላልፍ ነበር በማለትም መልስ ሰጥቷል።

ግብረአበር የለውም ለሚለው የጠበቆች መከራከሪያን በሚመለከትም መልስ የሰጠው ፖሊስ÷ ለሽብር ተግባር ዓላማ የሚዲያ ክንፍ በመጠቀም የግጭት ቀስቃሽ የሽብር መልዕክቶችን ለተከታዮቹ በማሠራጨቱ ምክንያት ጦርነት በማንሳት በሀገሪቱ ላይ ጉዳት ለማድረስ የተዘጋጁበት ሁኔታ አለ ሲል ገልጿል።

በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ በተሰራጩ የሽብር ቀስቃሽ መልዕክቶች መነሻ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት አለ በማለት ጠቅሷል።

ተጠርጣሪው ቢወጣ ከተከታዮቹ ጋር በመሆን ከፍ ያለ ጉዳት እንዲደርስ እና ሀገሪቱም ያለመረጋጋት ሁኔታ ውስጥ እንድትገባ ሊያደርግ ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል።

የግራ ቀኙን ክርክር እና የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን የተመለከቱት ዳኛ ከቀሪ ምስክሮች አሰማም እና ከቀሪ ምርመራ ሥራ አንጻር ለፖሊስ የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜ መሥጠት እንደሚያስፈልግ ድምዳሜ ላይ በመድረስ የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ አለመቀበላቸውን አብራርተዋል።

በዚህም መሠረት ለመርማሪ ፖሊስ የዘጠኝ ቀናት የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.