Fana: At a Speed of Life!

ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ ለወጣቶች ትኩረት መስጠት ይገባል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም እና ልማት ለማረጋገጥ ለወጣቶች ትኩረት መስጠት ይገባል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

የ2015 ዓ.ም የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድና የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር “በጎነት ለኢትዮጵያ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል፡፡

በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ ወጣትነት ፈርጀ ብዙ ፍላጎቶች የሚንፀባረቁበት የእድሜ ክልል ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ ወጣቶች አፍላ ጉልበታቸውን እና አቅማቸውን ማህበረሰብን በመርዳት ሲያውሉ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት እና እድገት ድርሻው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።

ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወኑ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በክረምት በጎ ፈቃድ የሚሰሩ ተግባራት የመንግስትን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያስቀራሉ ያሉት ሚኒስትሯ÷ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ ለወጣቶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በ2015 የበጎ ፈቃድ እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ወጣቶች ተሳትፎ እንዲያደርጉ እና በሀገሪቱ በሚከሰቱ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሚዲያዎች እና ባለድርሻ አካላት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቅናቄን በመፍጠር፣ አፈፃፀሙን በመከታተል እና በማገዝ የወጣቶችን ጥረት እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡

በሚኪያስ አዬለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.