በመዲናዋ የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት ልማት ፕሮግራም እየተተገበረባቸው የሚገኙ ት/ቤቶች ተጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት ልማት ፕሮግራም እየተተገበረባቸው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ጎብኝተዋል፡፡
ለሕጻናት ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ የሚባሉ ጊዜያት ላይ አተኩሮ የሚሠራው የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት ፕሮግራም በአዲስ አበባ ከተማ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
መርሐ-ግብሩ ÷ ከእናቶች እርግዝና ጀምሮ ለእናቶች ምክር በመሥጠት ፣ ከወለዱ በኋላም የልጆቻቸው አመጋገብና እንክብካቤ ላይ ማድረግ ያለባቸውን ሳይንሳዊ ሂደት ግንዛቤ በመፍጠር ነው እየተተገበረ የሚገኘው።
አቶ ጃንጥራር አባይ ÷ በትምህርት ቤቶች የሕጻናት የትምህርት አሰጣጥና እንክብካቤ ምን እንደሚመስልም በዛሬው ዕለት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተተገበረ ያለው በጨዋታ መልክ የሚሰጥ ትምህርት ሕጻናት የትምህርት አቀባበላቸው እንዲጨምር የሚያስችል በመሆኑ በሁሉም የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ይስፋፋል ብለዋል ም/ከንቲባው።
በ2016 በጀት ዓመት በመንግስት መሥሪያ ቤቶች የሕጻናት ማቆያ ማዕከላት ግንባታ በሥፋት እንደሚከናወንም ተናግረዋል፡፡
አቶ ጃንጥራር አባይ÷ በንፋስ ሥልክ ላፋቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ኅንጻ ውስጥ ለሕጻናት ማቆያ የተገነባውን ማዕከልን መመረቃቸውንም የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።