2016 የበጀት አመት የሐረርን ታሪክ የሚመጥን ስራ ማከናወን ይገባል – አቶ ኦርዲን
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 የበጀት አመት የሐረርን ታሪክና ስልጣኔ ሊመጥን የሚችል የከተማ ልማት ስራ ማከናወን ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡
የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ÷ በክልሉ በ2016 በመንግስት የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በሌሎች አጀንዳዎች ላይ መክሯል።
በ2016 የበጀት አመት የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ለክልሉ ነዋሪዎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የክልሉን ኢኮኖሚ የበለጠ ለማነቃቃት ሚናቸው የጎላ መሆኑን አቶ ኦርዲን ገልጸዋል፡፡
በእቅድ ላይ የተመሠረተ ስራን በማከናወን የክልሉን ህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን ማከናወን ቁልፍ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡
ፕሮጀክቶቹ የስራ እድልን የሚፈጥሩ፣ የከተማውን ፅዳትና ውበትን የሚያጎለብቱ እና ገቢን የሚያመነጩ ተግባራት ላይ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ሐረር ከተማን በእቅድ ለመምራት ክልላዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸው÷ የሐረርን ታሪክና ስልጣኔ ሊመጥን የሚችል የከተማ ልማት ስራ ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሕገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ ላይ የተጀመረውን የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራም በትኩረትና በቅንጅት ማስቀጠል ያስፈልጋል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የታቀዱ እቅዶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ከማድረግ አንፃር አመራሩና ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና በቁርጠኝነት እንዲቀሳቀሱ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡