በሱዳን ያለው ግጭት ተባብሶ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድ ጊዜ ጋብ ሲል ሌላ ጊዜ ሲፋፋም የሰነበተው የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ግጭት አሁንም በርዕሰ መዲናዋ ካርቱም የተለያዩ አካባቢዎች ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
የተፋላሚዎቹ ግጭት በዋናነት በምሥራቅ ካርቱም፣ ከባሕሪ በስተ ሰሜን እና ከኦምዱርማን በስተ ምዕራብ መፋፋሙን የዓይን እማኞች ለሲ ጂ ቲ ኤን ገልጸዋል።
ዛሬ በቡሪ አቅራቢያ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ግጭት በጦር አውሮፕላኖች ጭምር የታገዘ መሆኑንም ነው የዓይን እማኞቹ የተናገሩት፡፡
በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ የሞት እና የአካል ጉዳት ስለመኖሩ ባይጠቀስም÷ በበርካታ የቡሪ አካባቢዎች የመድፍ አረሮች እና ፍርስራሽ ሕንፃዎች እንደሚታዩ ተገልጿል፡፡
በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለምግብ እና ለንፁሕ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ስለመጋለጣቸውም ነው የተመለከተው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) 15 ሚሊየን የተቸገሩ ዜጎችን ለመርዳት 95 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ያስፈልገኛል ብሏል፡፡
በሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሪፖርቱን እስከአወጣበት ያሳለፍነው ረቡዕ ድረስ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ገልጿል፡፡