ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት ከቻይናው ዋይ ቲ ኦ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በዓመት 10 ሺህ ትራክተሮችን ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ለመገንባት ከቻይናው ዋይ ቲ ኦ ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እና የዋይ ቲ ኦ ካማኮ ሲኒየር ፕሮጀክት ማናጀር ዋንግ ሰን ተፈራርመዋል።
ፋብሪካው በሞጆ ከተማ የሚገነባ ሲሆን÷ ዋይ ቲ ኦ ኩባንያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታውን በማጠናቀቅ ወደ ስራ እንደሚገባ ተመላክቷል።
ፋብሪካው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ በቀን 50 ትራክተሮችን እና በዓመት ከ10 ሺህ በላይ ትራክተሮችን የማምረት አቅም ያለው መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታወጣውን የውጪ ምንዛሪ በማስቀረትና የውጪ ምንዛሪን በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚያበረክት ተገልጿል፡፡
በበረከት ተካልኝ