በሰሜን ሸዋ ዞን የህብረተሠቡን ሠላም ለማናጋት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የጥፋት ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ሸዋ ዞን ከነፍስ ወከፍ እስከ ቡድን መሣሪያ ዲሽቃ በመታጠቅ የህብረተሰቡን ሠላም ለማናጋት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የጥፋት ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
የጥፋት ቡድኑ አባላት በዞኑ ፀጥታ ኃይልና በመከላከያ ሠራዊቱ የተቀናጀ ዘመቻ እኩይ ዓላማቸውን ለመፈፀም እየተማከሩ ባሉበት ነው በድንገት በቁጥጥር ስር የዋሉት።
በቁጥጥር ሥር የዋሉት የቡድኑ አባላት ቁጥር 25 ሲሆን÷ ከዚህ ቀደም የመከላከያ ሠራዊትና የልዩ ኃይል አባል የነበሩ በኅቡዕ ሴራቸውን ለማስፈፀም በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ተታለው ጫካ የገቡ ወጣቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን የፀጥታ ኃይል ክትትል እያደረገ ባለበት ወቅት የጥፋት ቡድኑ አባላት ተኩስ በመክፈታቸውና የከፋ ጉዳት ሊያደርሱ በመሆኑ በቀጠናው ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት አስቸኳይ ሪፖርት በማድረግ በፍጥነት በቦታው ላይ በመድረስ መቆጣጠር መቻሉ ተጠቁሟል፡፡
የሠላም ፀር የሆኑ እነኝህ የቡድኑ አባላት የግለሰብ ቤት በመከራየት በሚሰጣቸው ተልዕኮ መሠረት የጥፋት ተግባራቸውን ለመፈፀም 1ዲሽቃ፣ 2 ብሬን ፣4 ስናይፐር ፣5 ክላሽ፣ 2 ሽጉጥና ከ2 ሺህ 300 በላይ ተተኳሽ ጥይቶችን እንዲሁም ጥሬ ገንዘብና በባንክ አካውንት ላይ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ድረስ ይዘው ሲንቀሳቀሱ ነው የተያዙት፡፡
የጥፋት ቡድኑን አባላት በፈጣን ክትትል መቆጣጠር ባይቻል ኖሮ በሕብረተሰቡ ላይ ጥፋት ያደርሱ እንደነበር የገለፁት የፀጥታ ኃይል አባላት÷ የሕዝቡን ሠላም ለማስጠበቅ አበክረው እየሰሩ እንደሆነ መናገራቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡
በሕግ ጥላ ሥር የዋሉት ግለሰቦችም አብዛኞቹ ተታለው እንደገቡና ሕገ ወጥ አደረጃጀት ፈጥረው መንቀሳቀሳቸውን በማመን ወጣቶች ከእንደዚህ ዓይነቱ ዓለማ ከሌለው ተግባር መቆጠብ እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።