Fana: At a Speed of Life!

ቻይና በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማትን ለማሳደግ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማትን በማሳደግ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጻለች፡፡

የኢትዮጵያ፣ የቻይና መንግስት እና የተመድ የልማት ፕሮግራም የባዮጋዝ፣ የባዮማስ እና የፀሐይ ኃይል የደቡብ ደቡብ የሶስትዮሽ የልማት ትብብር ማዕቀፍን መሰረት ያደረገ አዲስ የፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርመዋል።

በሶስትዮሽ የትብብር ስምምነቱ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር ኢ/ር) ÷ የቻይና መንግስት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ተወካዮች ተገኝተዋል።

ሱልጣን ወሊ ((ዶ/ር ኢ/ር) ÷ ስምምነቱ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና አካባቢው፣ በሐረር ከተማ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በአማራ ክልል በባዮ ጋዝ፣ በፀሐይ ኃይል የታዳሽ ኃይል ልማት ለማካሄድ የሚያስችል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በስምምነቱ መሰረት የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ስራውን የሚያግዝ የምርምር ማዕከል ለማቋቋም እና የተመራማሪዎችን አቅም ለማጎልበት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና የንግድ ካውንስለር ያንግ ይሀንግ÷ ቻይና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከአፍሪካ ጋር በዘርፈ ብዙ የልማት መስኮች በትብብር እየሰራች ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያም የታዳሽ ኃይል የምርምር ማዕከል ለማቋቋም እና የታዳሽ ኃይል አማራጭ ልማትን ለማስፋት የተደረሰው የሶስትዮሽ ስምምነት የዘርፉን እድገት ለመደገፍ መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ልማትን በማስፋት የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ቻይና በጠንካራ የፖሊሲ እርምጃ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

በተመድ  የልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ክሊዮፋስ ቶሮሪ÷ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ልማትን ማስፋት የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

የሶስትዮሽ የትብብር ስምምነቱም በባዮ ማስ፣ ባዮ ጋዝ እና በፀሐይ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ልማትን ለማስፋት እንደሚያግዝ ማስገንዘባቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.