የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የስራ መልቀቂያ አስገቡ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ “ጤናየን በሚገባ ለመጠበቅ የረጅም ጊዜ እረፍት ያስፈልገኛል” በማለት በፈቃዳቸው የሥራ መልቀቂያ አስገቡ፡፡
በዚህም “ከ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነቴ በገዛ ፈቃዴ መልቀቄን ለተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ጽሕፈት ቤት ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም አሳውቄያለሁ” ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
“ማሕበረሰቤን የማገልገል እድል እንዳገኝ ቦርዱን በሰብሳቢነት ለመምራት በእጩነት ላቀረቡኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዲሁም እምነቱን ጥሎ ኃላፊነቱን ለሰጠኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል፡፡
“የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ቦርዱን እንደ አስተዳዳሪ እና እንደተቆጣጣሪ ከማየት ይልቅ በጋራ እንደሚሰራ ቤተሰብ በመቁጠር የማያስደስታቸውን ውሳኔ በምንወስንበት ወቅት ጭምርም እምነታቸውን ስላልነሱን አመሰግናለሁ” ነው ያሉት፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በጉዳዩ ላይ ብርቱካን ሚደቅሳ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ያደረገው የስልክ ሙከራ ባለማንሳታቸው ምክንያት አልተሳካም፡፡
በቀጣይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የሚያወጣው ዝርዝር መረጃ ካለ ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል፡፡
በ2011 ዓ.ም ታኅሣሥ ወር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡