Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7 ነጥብ 5 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል – ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በተያዘው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ 7 ነጥብ 5 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገለጹ፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ( ዶ/ር )ከአሜሪካ ንግድ ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 3 ነጥብ 31 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መገኘቱንም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተቀባይ መሆኗንም ጠቅሰዋል፡፡

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አንድ የተገኙ ተሞክሮዎችና ውጤቶች እንዲሁም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሁለት ዝግጅትና ይዘት እንዲሁም በአጠቃላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ገለጻ አድርገዋል።

የኮቪድ-19 ተጽዕኖ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰቱ ግጭቶች፣ የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት፣ በአየር ንብረት ምክንያት የተከሰቱ አደጋዎች፣ ጎርፍ፣ ድርቅ እና የበረሃ አንበጣ ኢኮኖሚውንና አጠቃላይ ሀገሪቱን የፈተኑ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

እነዚህ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዓመታዊ ዕድገት እያስመዘገበ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

ኢኮኖሚውን ከነበሩበት ውስብስብ ችግሮች ለማላቀቅ ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን ማድረግ አንዱ ውጤታማ ሥራ እንደነበር ተናግረዋል።

የንግድ ሕግ፣ የንግድ ምዝገባ እና የንግድ ፈቃድ ፣ የተንቀሳቃሽ ንብረት ደኀንነት መብት አዋጅ ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያን ጨምሮ 11 ፖሊሲዎችና ሕጎች መሻሻላቸውንና መከለሳቸውን አብራርተዋል።

በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በቢዝነስ አመቺነት፣ በታክስ ስርዓት ፣ በኃይል አቅርቦትና በማዕድን ፣ በቱሪዝም በአይ ሲ ቲ፣ በግብርናና ማኑፋክቸሪን እንዲሁም በሌሎች መስኮች ተጨባጭ ለውጦች በሪፎርሙ መምጣታቸውን አብራርተዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሁለትን ይዘትና ዝግጅት በተመለከተም ማብራሪያ የሰጡት ፍጹም (ዶ/ር) ሪፎርሙ ኢኮኖሚን ለማጎልበት የሚያግዙ አራት ዋና ዋና ምሰሶዎች አሉት ብለዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን መፍጠር፣ ምቹ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ሁኔታን መፍጠር፣ የቁልፍ ዘርፎች ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም አቅም ያለው እና ቀልጣፋ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት በሪፎርሙ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኩባንያዎች ቢሰማሩ በርካታ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዳሉ ገልጸው÷ በግል፣ በመንግስትና የግል አጋርነት እንዲሁም በሽርክና ሊሰሩባቸው የሚችሉ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.