ርዕሳነ መስተዳድሮች ለዓረፋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ነገ ለሚከበረው 1 ሺህ 444ኛው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በመልዕክታቸው÷ የኢድ አል አድሃ በዓልን ለተቸገሩ ወገኖች ማዕድ በማጋራት እና የተቸገሩትን በመርዳት ልናከብረው ይገባል ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በመልዕክታቸው÷ የኢድ አል አድሃ በዓልን ለተቸገሩ ወገኖች ማዕድ በማጋራት እና የተቸገሩትን በመርዳት ልናከብረው ይገባል ብለዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው ÷ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሕዝበ-ሙስሊሙ የጋራ አንድነቱን በማጠናከር ዕምነቱ በሚያዘው መሠረት አቅመ ደካሞችን በመርዳት እና ለሌላቸው በማካፈል በዓሉን እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዓሉን ስናከብር ፈተናዎችን ሁሉ በጽናት በማለፍ፣ መልካም ነገር በመፈጸም፣ ለአካባቢያችን ሰላምና ጸጥታ መስፈን የድርሻችንን በመወጣት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በዓሉ የሰላም የፍቅርና የደስታ በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ባስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል-አደሃ በዓልን ሲያከብር÷ የተቸገሩ ወገኖችን በማብላትና የተጠሙትን በማጠጣት የተለመደ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባህሉን በመተግበር እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል።
ሕዝበ ሙስሊሙን ጨምሮ መላው የክልሉ ነዋሪም ÷ ሰላምን፣ አብሮነትን፣ መተባበርንና ወንድማማችነትን በማጎልበት በክልሉ እየተከናወኑ ለሚገኙ የልማት ተግባራት ድጋፉን እንዲያጠናክር ተጠይቋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ባስተላለፉት መልዕክት የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል በፍቅር እና በአንድነት እንዲከበር ሕዝበ ሙስሊሙ ወንድማማችነቱን መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡
አገር፣ ቤተሰብ፣ ልማትና እድገት የሚኖረው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ለሰላም ከፍ ያለ ዋጋ በመስጠት በሰዎች መካከል የትብብርና ወንድማማችነት መንፈስ ማስፈን እንደሚገባ ገልፀዋል።