የመውጫ ፈተና ከፊታችን ሐምሌ 3 እስከ 8 ይሰጣል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዎች የመውጫ ፈተና ከሐምሌ 3 እስከ 8 2015 ዓ.ም እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የትክክለኛ ተፈታኞችን ቁጥር እንዲያጣራ በማድረግ÷ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 95 ሺህ 755 እንዲሁም ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች 74 ሺህ 776 ተማሪዎች ለፈተና ይቀመጣሉ፡፡
ፈተናውን ያላለፉ ተማሪዎቸ ዲግሪ እንደማይሰጣቸው እና የትምህርት ሚኒስቴር በሚያዘጋጀው የፈተና ጊዜ መሰረት ድጋሚ እንደሚፈተኑ ተመልክቷል፡፡
የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎችን እውቀትና ብቃት ለመለካት የሚሰጠው የመውጫ ፈተና ዝግጅት መጠናቀቁን በሚኒስቴሩ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ ኢዮብ አየነው (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ገበያው የሚፈልገውን ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የመውጫ ፈተናው ከ2015 ጀምሮ በሁሉም የትምህርት መስኮችና መርሐ ግብሮች መስጠት እንዲቻል ስራዎች ከአንድ ዓመት በላይ ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ከተማሯቸው የትምህርት ዓይነቶች መካከል÷ መሰረታዊ የሚባሉ ከ12 እስከ 17 የትምህርት ዓይነቶች ፈተና እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የፈተና ንድፍ እና የብቃት መመዘኛ መስፈርቶች መዘጋጀታቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
ከግንቦት 15 ጀምሮ ለ211 የትምህርት ፕሮግራሞች የፈተና ጥያቄዎች በማውጣት ለፈተናው ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ እንዲሆን መደረጉን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡
ፈተናው በኦንላየን የሚሰጥ በመሆኑም አስፈላጊ የቴሌኮም እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
በሀገሪቱ ካሉ 325 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 161 እና ከመንግስት ደግሞ 44 ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን እንደሚያስፈትኑ ጠቅሰዋል።