የአፍሪካ ባለሐብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋሉ – ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ባለሐብቶች በኢትዮጵያ ባሉ የግብርና እና የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ገለጹ፡፡
የኢንዱትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ከተመራው ልዑክ ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡
አቶ መላኩ አለበል በውይይታቸው ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ዕድሎች ገልጸውላቸዋል፡፡
በቀረቡት የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይም ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪማቅረባቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለማሳካት የወጠነችውን የ10 አመት ዕቅድ ለመፈጸም እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን አንስተዋል፡፡
በአምራች ኢንዱስትሪ ለሚሠማሩ ባላሐብቶች አስፈላጊ ድጋፍ እና ማበረታቻ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
ከሌሎች ሀገራት በተወሰደው ተሞክሮ መሠረት የተጀመረው “የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” አበረታች ውጤቶችን ማስገኘቱን አስገንዝበዋል፡፡
ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ይህን ንቅናቄ ተግባራዊ ቢያደርጉ በዘርፉ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ነው ያመላከቱት፡፡
ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እያደጉ ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ መሆኗን አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ ባለሐብቶች በሀገሪቱ ባሉ የግብርና እና የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡