የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ተወሰነ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዲሱ ክልል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከትናንት ጀምሮ እያካሄደ ነው፡፡
በዛሬው ውሎውም የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተካተቱበት «የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል» በሚል ስያሜ አዲስ 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ቀድሞ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይኖሩ የነበሩ የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባካሄዱት ሕዝበ ውሳኔ በአንድ ክልል የመደራጀት ፍላጎታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በአንድ ክልል እንዲደራጁ በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ወስኗል፡፡
«የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል» በሚል በአዲስ የተደራጁት በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጎፋ፣ በጌዴኦ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በኮንሶ ዞኖችና በደራሼ፣ በቡርጂ፣ በአማሮ፣ በኧሌና በባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው፡፡
ቀድሞ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል ውስጥ የነበሩ የሀድያ፣ የሀላባ፣ የከምባታ ጠምባሮ፣ የስልጤ፣ የጉራጌ ዞኖችና የየም ልዩ ወረዳ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚቀጥሉ ይሆናል።
ውሳኔው በሙሉ ድምጽ መጽደቁን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡