ቻይና÷ አሜሪካ ለታይዋን የጦር መሣሪያ እንዳትሸጥ ተቃወመች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ለታይዋን የጦር መሣሪያዎችን ልትሸጥ አይገባም ስትል ቻይና በጽኑ ተቃውማለች፡፡
ባሳለፍነው መጋቢት ወር አሜሪካ የ619 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የጦር መሣሪያዎችን ለታይዋን ለመሸጥ ማጽደቋ ይታወሳል፡፡
የቻይና የመከላከያ ሚስቴር ቃል አቀባይ ታን ኬፌይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ አሜሪካ ከታይዋን ጋር ያላትን ወታደራዊ ግንኙነት በአስቸኳይ እንድታቋርጥ አሳስበዋል፡፡
የቻይና እና የታይዋን ጉዳይ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ አሜሪካ ጣልቃ ገብታ ውጥረቱን ከማባባስ እንድትታቀብ ጠይቀዋል፡፡
የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት የአንድ ቻይናን መርኅ የሚጥስና ሦስቱን የቻይና-አሜሪካ የጋራ የግንኙነት ድንጋጌዎች ያላገናዘበ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል፡፡
የቻይና ጦር ማንኛውንም ትንኮሳ ለመመከት ዝግጁ ስለመሆኑ ማረጋገጣቸውን ጠቅሶ ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡