Fana: At a Speed of Life!

ዘላቂ የልማት ግቦቹን ለማሳካት ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጥረቱን በእጥፍ እንዲያሳድግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጥረቱን በእጥፍ እንዲያሳድግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠየቀ፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተፅዕኖዎች፣ በሩሲያና ዩክሬን መካከል የዘለቀው ግጭት እንዲሁም የተዛነፈ የኢኮኖሚ አተያይ በፈረንጆቹ 2015 ላይ የተዘረዘሩት ዘላቂ የልማት ግቦች በተፈለገው ልክ እንዳይሳኩ እንቅፋት መሆናቸውን ተመድ ጠቁሟል፡፡

ተመድ በሪፖርቱ አሁንም በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚስተዋሉት ተፅዕኖዎች ባሻገር የዓለም መንግስታት እራሳቸው ያመላከቷቸውን ዘላቂ የልማት ግቦች እንዲተገብሩ ጠይቋል፡፡

ይህ ሳይሆን ቢቀር ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋትን ሊከሰት እንደሚችል ያስጠነቀቀው ተመድ፤ ግቦቹ እስከ ፈረንጆቹ 2030 የዓለም አቀፉ የልማት ጥረቶች ንድፍ ሆነው እንዲያገለግሉ መንግስታቱ በአንድ ድምፅ መቀበላቸውንም ሲጂቲ ኤን አስታውሷል።

ከተዘረዘሩት ግቦች 17ቱ ድኅነትን ለማስወገድ፣ እኩልነትን ለማስፈን እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያለሙ መሆናቸው ይታወቃል።

አሁን ያለው አዝማሚያ በዚሁ ከቀጠለ በፈረንጆቹ 2030 ላይ 575 ሚሊየን ያኅል ሰዎች በከፋ ድኅነት ውስጥ እንደሚቆዩ እና 84 ሚሊየን የሚገመቱ ሕጻናትና ወጣቶች ከትምህርት ገበታቸው እንደሚስተጓጎሉ ተመድ አመላክቷል።

በ2023 የወጣው ልዩ ዘላቂ የልማት ግቦች ሪፖርት ግቦቹ የማይተገበሩ ከሆነ ዓለማችን ወደ ማይቀለበስ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ልታመራ እንደምትችል አስጠንቅቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.