Fana: At a Speed of Life!

ለሽብር ተግባር 50 የእጅ ቦምብና 58 የቦምብ ፊውዝ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሽብር ተግባር የሚውል 50 የእጅ ቦምብና 58 የቦንብ ፊውዝ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ከሰዓት በኋላ በነበረው ቀጠሮ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ያቀረበውን የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄና የተጠርጣሪዎችን መከራከሪያ ነጥብ ተመልክቷል

ተጠርጣሪዎቹ አብዱ መላኩ ቡሾ፣አማኑኤል ግርማ ተሲሳ እና ደጋጋ ፈቀደ ወለጋ ናቸው።

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት በተፈረጀው ሸኔ የሽብር ቡድን የአባልነት መታወቂያ በመያዝ፣ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ በመገናኘት፣ ተልዕኮ በመቀበል፣የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን እና አልባሳትን በማቀበልና በአዲስ አባባ የሚገኙ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችን ለመግደል እና ለማስገደል በማቀድ የሽብር ቡድኑን አላማ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ጠቅሶ ለችሎቱ አብራርቷል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 14 ተከራይተው ከሚኖሩበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ለሽብር ተግባር የሚውል 50  (ኤፍ 1) የእጅ ቦምብና  58  የቦምብ ፊውዞችን በማውጣት  ቄለም ወለጋ ለሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኑ አባላት ለማቀበል ሲንቀሳቀሱ በተደረገ ክትትል ሐምሌ 7 ቀን 2015 ዓ.ም እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን አንስቷል፡፡

ይህን መነሻ በማድረግ በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 59/2 መሰረት የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

አንደኛ ተጠርጣሪ ምንም ወንጀል አልፈጸምኩም በማለት ተከራክሮ የዋስትና መብቱ እንዲከበር ጠይቋል።

በዚህ ጊዜ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን በሚመለከቱት ዳኛ በኩል ቦምቦቹ በ1ኛ ተጠርጣሪ መኖሪያ ቤት ተቀምጠው እንደነበር እና እንዳልነበር  የማረጋገጫ ጥያቄ ጠይቀዋል፡፡

ተጠርጣሪውም በመኖሪያ ቤቱ ቦምቡ ተቀምጦ እንደነበር በመግለጽ÷ ቦምብን ግን 2ኛ ተጠርጣሪ ማስቀመጡን ጠቅሶ ሌላ ዕቃ እንጂ  ቦምብ አልመሰለኝም በማለት ለችሎቱ ገልጿል።

ሁለተኛ ተጠርጣሪ ደግሞ ቦምቦቹን ሌላ ነጋዴ ጓደኛው በፔስታል ውስጥ ከቶ እንደሰጠው  ገልጾ÷የዋስትና መብቱ እንዲፈቀድለት ጥያቄ አቅርቧል።

ሶስተኛ ተጠርጣሪ በበኩሉ÷ ተማሪ መሆኑን ጠቅሶ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት የለኝም በማለት ፍርድ ቤቱ ዋስትና  እንዲፈቅድለት ጠይቋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪዎቹ ቦምቦቹን ይዘው እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን በመግለጽ በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ፍተሻ ደግሞ ተጨማሪ የሽብር ቡድኑ የአባል መታወቂያ ማግኘቱን አብራርቷል።

መርማሪው አክሎም በትግል ስሙ አዱኛ ተስፋዬ የሚባልና በሌላ ስሙ ደግሞ ነጋሴ ምሬሳ የተባለ አንድ የሸኔ አመራር ከቄለም ወለጋ ለ2ኛ ተጠርጣሪ ስልክ በመደወል ከአዋሽ አፋር የሚመጣ ዕቃ ተቀብሎ እንዲልክለት መልዕክት መላኩን የሚገልጽ ማስረጃ መገኘቱንም ጠቅሷል፡፡

ቦምቦቹ የተያዙት በሶስቱም ተጠርጣሪዎች እጅ  ከፍንጅ ነው ወይ?  በማለት በመዝገቡን በሚመለከቱ ዳኛ የተጠየቀው ፖሊስ፣አዎ እጅ ከፍንጅ ነው የተያዙት በማለት መልስ ሰጥቷል።

የተጠረጠሩበት ወንጀል ውስብስብ እና ሕዝብና መንግስትን ለአደጋ የሚጥል የሽብር ተግባር መሆኑን በመጥቀስ እንዲሁም ምስክር ሊያሸሹ ይችላሉ በማለት ስጋቱን ገልጾ ፖሊስ የዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም ተከራክሯል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱም ተጨማሪ የማጣሪያ ምርመራ ስራ መከናወን እንዳለበት በማመን ለፖሊስ የ14 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.