Fana: At a Speed of Life!

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሰራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሰራተኞች በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ላይ ተሳትፈዋል፡፡

በጅማ ዞን ማና ወረዳ አረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ÷ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሩ ሕዝቡ ከተባባረ ብዙ ነገር መለወጥ እንደሚችል ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

መርሐ ግብሩ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚመጡ ተያያዥ ችግሮችን ከመከላከል ባለፈ የሕዝቡን አንድነት አጉልቶ ያሳየ እንደሆነም ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ ”ዛሬ በጅማ ዞን የታየው የህዝቡ ንቅናቄና ለአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ያሳየው ተነሳሽነት ያለንን ትብብርና አንድነት የሚገልጽ ነው” ብለዋል።

በተመሳሳይ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አመራር እና ሠራተኞች በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

በዚሁ ወቅት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር  ወርቁ ጋቸና (ኢ/ር)÷ የሚተከሉት ችግኞች የደን ሽፋንን በመጨመር በኩል የማይተካ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በመተከል ላይ የሚገኙት ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን በቀጣይ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሀገርንና ሕዝብን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብርን በትብብር መሥራት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.