የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ተፈጥሮን የመጠበቅ ባህል በሌሎችም መለመድ አለበት – አለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ ያለው ተፈጥሮን የመጠበቅ ባህል በሌሎች ዘንድም መለመድ ይኖርበታል ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ በትናንትናው ዕለት በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ተገኝተው በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ላይ አሻራቸውን አኑረዋል።
በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግርም ፥ የተተከሉ ችግኞችን መልሶ ማየትና መጠበቅ የሁሉንም ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን አንስተዋል።
የሚተከሉ ችግኞች የተተከሉበት ዓላማ እንዳላቸው በመጥቀስም፥ የተተከሉለትን ዓላማ ማሳካት የሚቻለው ህጻናትንና እንስሳትን እንደምንከባከበው ችግኞችን መንከባከብ ስንችል ነው ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ደንን የመጠበቅ የዳበረ ባህል ያላቸው ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ ፥ ደንን ጠብቀው ያቆዩት የሚያገኙትን ጥቅም ስላወቁ ነው ሲሉም ነው አድናቆታቸውን የገለጹት።
በዚህም ይህ ባህል በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች መለመድ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው ፥ “የወለድነውን ልጅ ወልደን እንደማንተው ሁሉ የተከልናቸውን ችግኞች እንዲሁ ተንከባክቦ ማሳደግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው” ብለዋል።
ችግኝ ለመትከል የተደረገው ዘመቻ የተተከሉትን በመንከባከብ ለመድገም ይሰራል ሲሉም ነው ያስገነዘቡት።
በተስፋየ ምሬሳ