Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ በቀጣይነት እንዲተገበር ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ህዝብን በማሳተፍ የመሰረተ ልማት ግንባታና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል ድጋፍና ክትትል ሲያደርግ የቆየው የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን ከክልሉ አመራሮች ጋር ዛሬ ውይይት አድርጓል።

አመራሮቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ከሐምሌ 1 እስከ 10/2015 ዓ.ም በክልሉ ድጋፍና ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በኦሮሚያ ክልል የተንቀሳቀሰውን የአመራሮች ቡድን ያስተባበሩት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ በክልሉ ውጤታማ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መታዘባቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የህዝቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ለዚህም የክልሉ አመራርም ሆነ በየአካባቢው ያለው ህዝብ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የአመራር ቡድኑ በተንቀሳቀሰበት ጅማ ዞን መመልከታቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይም በአመራሩና በሕዝቡ በኩል እየታየ ያለው የልማት ተነሳሽነትና ዘላቂ እንዲሆን በትኩረት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሌላው በክልሉ በተደረገ ድጋፍና ክትትል ላይ የተሳተፉት የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድርም (ዶ/ር) በሄዱበት አካባቢ ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎችን መመልከታቸውን አውስተዋል።

በተለይ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በክልሉ መንግስት የተቀረጹ የተለያዩ የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮች በአግባቡ እየተተገበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህንኑ የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ አርሶ አደሩ በየአካባቢው በኩታ ገጠም ተደራጅቶ በልማት ውስጥ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸው፥ ይህም ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ ነው ብለዋል።

በጎበኟቸው አካባቢዎች የአካባቢውን የልማት አቅም መሰረት ያደረጉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መመልከታቸውን የገለጹት ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ዘካሪያስ ሂርቀሎ ናቸው።

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የድጋፍና ክትትል ስራዎችን ማከናወናቸውን ገልጸው ፥ በአካባቢው ገበያ ተኮር ምርቶች በስፋት የማምረት ሥራው መጠናከሩን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ልማት በመቀየር ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር የተጀመረው ስራም የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የፌደራል መንግስት ክፍተኛ አመራሮቹ የተመለከቱት ነገር በአመዛኙ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም አሁንም በየአካባቢው የመሰረተ ልማት ፍላጎቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ በምርታማነት በኩል የተሻለ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸው ፥ የገበያ ትስስር ችግር እንዳለም መታዘባቸውን ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው፥ የአመራሮቹ ጉብኝት በክልሉ እየተመዘገበ ካለው ስኬት ባሻገር ጉድለቶችን ለማረም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በግብርና ልማት በኩል ሰፋፊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው ፥ በአመራሮቹ በኩል ልማቱን የበለጠ ለማስፋፋት የሚረዱ ገንቢ አስተያየቶች መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮም እንደ ክፍተት የተነሱ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ለበለጠ ለውጥ እንደሚተጋ አስታውቀዋል።

በውይይቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.