Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል ጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ጉዳት እንዳያስከትሉ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በክረምቱ ምክንያት የሚከሰቱ የጎርፍ፣ ናዳ እና መሬት መንሸራተት አደጋዎች ጉዳት እንዳይደርሱ በተለይም ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የክልሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

ለጎርፍ፣ ናዳ እና መሬት መንሸራተት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ጉዳት እንዳይደርስ ግብረኃይል ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጋንታ ጋምአ ተናግረዋል፡፡

ማረቆ፣ ምስራቅ መስቃን፣ መስቃን፣ ስልጢ፣ ሳንኩራ፣ ምስራቅ ስልጢ፣ ሻሾጎ፣ የሀላባ ዞን ሦስቱም ወረዳዎች እንዲሁም አበላ አባያ፣ ዱጉና ፋንጎ እና ሁምቦ ወረዳዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ናቸው ብለዋል፡፡

እንዲሁም ለጎርፍ ተጋላጭ ከሆኑት መካከል÷ አርባምንጭ ዙሪያ፣ ምዕራብ አባያ፣ አርባምንጭ ከተማ አስተዳደር፣ ዑባ ደብረ ፀሐይ፣ ደምባ ጎፋ፣ ኦይዳ ከተማ አስተዳደር፣ ሳውላ ከተማ አስተዳደር፣ ዳሰነች፣ ሐመር፣ ኛንጋቶም እና በናጸማይ ወረዳዎች ይገኙበታል ነው ያሉት፡፡

ገሬሴ፣ ቦንኬ ዲታ፣ ጨንቻ፣ ጋጮባባ፣ ዳራማሎ፣ ኪንዶ ዲዳዬ፣ ኪንዶ ኮይሻ፣ ካዎ ኮይሻ፣ ገዜ ጎፋ፣ መሎጋዳ፣ መሎ ኮዛ፣ ደቡብ አሪ፣ ሰሜን አሪ ወረዳዎች እንዲሁም አሌ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ደግሞ ለናዳና የመሬት መንሸራተት ተጋላጭ መሆናቸውን ነው ያነሱት፡፡

ከማረቆ ወረዳ ጀምሮ በጥናት ችግሮችን የመለየት ሥራ መከናወኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ÷ በተጋላጭ የጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሀዲያ እና ጋሞ ዞኖች የዳይክ ሥራ መሠራቱን አስረድተዋል፡፡

የኦሞ ወንዝ ዳሰነች ላይ ወረዳ ጉዳት እንዳያደርስ በፌደራል ተቋማት በኩል ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

በተጋላጭ አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖች የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን በመጠቀም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ነው ያሳሰቡት፡፡

የውሀ ስርገትን በመጨመር ጎርፍን ለመከላከል፣ የናዳና መሬት መንሸራተትን ለመቀነስና ለማስቀረት÷ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራን በማጠናከር የአፈርና ውሀ ጥበቃ ሥራን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ለናዳና መሬት መንሸራተት ተጋላጭ ከሆኑ የወላይታ፣ ጋሞ እና ጎፋ ዞኖች ነዋሪዎችን ወደሌላ ቦታ በማስፈር አራት አዲስ ቀበሌዎች በስጋትና በጉዳት በተፈናቀሉ ወገኖች መመስረቱን አስረድተዋል፡፡

በ2015 የበልግ ወቅት በተከሰተ ጎርፍ÷ በዑባ ደብረ ጸሐይ ወረዳ 21 ወገኖች ሕይወታቸው ማለፉን እና 2 ሺህ 167 መፈናቀላቸውን ተናግረዋል፡፡

በኮንሶ ዞን የስድስት ሰዎች ሕይወት በጎርፍ አደጋ ማለፉን እና ሳንኩራ እና ስልጢ ወረዳዎችን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች በሰብልና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.