አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ፕሬዚዳንት ካርል ስካው ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደር ብርቱካን ድርጅቱ ከምስረታው ጀምሮ ለኢትዮጵያ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው በኢትዮጵያ እና በዓለም ምግብ ፕሮግራም መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ መልካም ትብብር አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን በመጥቀስም፥ ድርጅቱ በኢትዮጵያ በግጭት እና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያፋጥንም ጥሪ አቅርበዋል።
የምግብ እርዳታን ላልተፈለገ ዓላማ ከማዋል ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ የተጀመረውን ምርመራ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ነው አምባሳደር ብርቱካን የገለጹት።
የምርመራው ሂደት ባለበት ሆኖ ድርጅቱ ያቋረጠውን የምግብ እርዳታ አቅርቦት እንዲጀምርም ጠይቀዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ፕሬዚዳንት ካርል ስካው ድርጅቱ ያቋረጠውን የምግብ እርዳታ ምርምራው እየተካሄደ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል።
የምግብ እርዳታ ስርጭቱ ይበልጥ ግልጽነት በተሞላበት መንገድ ማከናወን የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋት እና እርዳታው ላልተፈለገ አላማ እንዳይውል ማድረግ ይገባል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።