Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት እንዲያበቃ ማድረግ በአፍሪካ ‘ህይወት ማዳን’ ማለት ነው – አዛሊ አሱማኒ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ- ዩክሬን ግጭት እንዲያበቃ ማድረግ በጥቁር ባህር በኩል ወደ ውጭ በሚላኩ እህል እና ሌሎች ምርቶች ላይ ጥገኛ የሆኑ ሰዎችን ህይወት ማዳን ማለት ነው ሲሉ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የኮሞሮሱ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ በሴንት ፒተርስበርግ እየተካሄደ ባለው የሩስያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር በሩሲያና ዩክሬን መካከል ሰላማዊ አብሮነት መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

በፈረንጆቹ 2022 የተደረሰው የእህል ማጓጓዝ ስምምነት ወደ ተግባራዊነቱ መመለስ እንዳለበትም ጠቁመው፤ ግጭቱ ከቀጠለ የሚያስከትለው አደጋ የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ የሆኑትን ለመታደግ መፍትሄ መፈለግ አለብን ማለታቸውን አር ቲ ዘግቧል።

በአቅርቦት መቆራረጥ ምክንያት በተፈጠረው አስደንጋጭ የምግብ ዋጋ መጨመር የአፍሪካ አህጉር ክፉኛ መጎዳቱን ገልጸዋል።

”ከሩሲያና ዩክሬን እህል እና የማዳበሪያ ደህንነቱ ተጠብቆ ወደ አህጉራችን እንዲደርስ ባለድርሻ አካላት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥሩ እንጠይቃለን” ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ስጋቷ ከተፈታ በጥቁር ባህር እህል ለሟጓጓዝ ወደተደረሰው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመመለስ ዝግጁ ነች ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.