Fana: At a Speed of Life!

ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ የወንጀል ክሶች ቀረቡባቸው

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ የወንጀል ክሶች ቀረቡባቸው።

ትራምፕ በፍሎሪዳ መኖሪያ ቤታቸው በሚገኝ የደህንነት ካሜራ የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምስልን በቤቱ የሚገኝ ‘የጥገና ባለሙያ እንዲያጠፋው አስገድደዋል’ በሚል ተጨማሪ ክስ እንደቀረበባቸው ቢቢሲ እና አልጀዚራ አስነብበዋል።

የእርሳቸውን ትዕዛዝ ተከትሎም ከዚህ ቀደም የአሜሪካን ከፍተኛ ሚስጥራዊ ሰነዶችን በአግባቡ አልያዙም በሚል ከቀረበባቸው ክስ ጋር በተያያዘ ማስረጃ ሊሆን ይችላል የተባለ ተንቀሳቃሽ ምስል ከካሜራው እንዲጠፋ ተደርጓል ነው የተባለው።

አዲስ የቀረበው ክስም የሚደረገውን የምርመራ ሂደት ለማስተጓጎል በመሞከር፣ የሀገሪቱ የመከላከያ ሰነዶችን ሆን ብለው በመያዝ እንዲሁም መረጃና ሰነዶችን አጥፍተዋል የሚል ሲሆን፥ ይህን ተከትሎም አጠቃላይ የቀረቡባቸው ክሶች 40 መድረሳቸው ተገልጿል።

ተንቀሳቃሽ ምስሉን በተቀበለው ትዕዛዝ እንዲጠፋ አድርጓል የተባለው ካርሎስ ደ ኦሊቬራ የተባለው የ56 አመት የጥገና ሰራተኛም፥ ከጉዳዮ ጋር በተያያዘ የፍትህ ሂደቱን ለማዛባት በማሴር፣ መርማሪዎችን በመዋሸት እና መረጃዎችን በማጥፋት ክስ እንደቀረበበት ዘገባው ያመላክታል።

ከእርሱ ቀደም ብሎ የቀድሞው የባህር ሃይል አባልና የትራምፕ የግል ጠባቂ የሆነው ዋልታ ናውታ በዚህ የክስ መዝገብ መካተቱ ይታወሳል።

የፌደራሉ መንግስት በሶስቱ ግለሰቦች ላይ የምርመራ ሂደቱን ለማደናቀፍ በማሴር፣ በመዋሸት እና ከፍተኛ ሚስጢራዊ መረጃዎችን ሆን ብለው በማጥፋት ክስ አቅርቦባቸዋል።

ትራምፕ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ምንም የሰሩት ጥፋት እንደሌላ በመጥቀስ የዐቃቤ ህጎችን ክስ ‘እብደት” ብለውታል።

የትራምፕ ጠበቆችም በጉዳዩ ላይ ከፌደራል ዐቃቤ ህግ ጋር የተገናኙ ሲሆን፥ ትራምፕም ጠበቆቻቸው ከዐቃቤ ህግ ጋር ‘ገንቢ ውይይት አድርገዋል’ ሲሉ ገልጸዋል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ ሰኔ ሁለተኛ ሳምንት ባለ49 ገጽ 37 አይነት ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።

በወቅቱ የቀረበባቸው ክስ የአሜሪካን የኒውክሌር ሚስጥር እና ወታደራዊ ዕቅዶችን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ሚስጥራዊ ሰነዶችን በአግባቡ አልያዙም የሚል ነበር።

ትራምፕ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ፍሎሪዳ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ‘የዳንስ ክፍል እና መታጠቢያ ቤት’ ውስጥ ደብቀው ማስቀመጣቸውም በቀረበባቸው ክስ እንደተጠቀሰም የሚታወስ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.