Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ 705 ሚሊየን 24 ሺህ ብር መገኘቱን የጋምቤላ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

 

የቢሮው ኃላፊ ኦባንግ ኦቻላ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ በመዳረሻዎች አካባቢ የሚገኙ 2 ሺህ 200 ሰዎች በቀጥታ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

 

በተጨማሪም ለ760 ሰዎች በሆቴል እና አስጎብኚነት ዘርፍ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

 

የዘንድሮው አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የሀገር ውስጥ ጎብኚ 2 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱን እና ውጭ ሀገር ደግሞ ባለበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

የተደራጀ የአካባቢ አስጎብኚ አለመኖር እንዲሁም በክልሉ አልፎ አልፎ የጸጥታ ችግር መኖር አፈጻጸሙን ከዚህ በላይ ማድረግ እንዳይቻል አድርጓል ነው ያሉት፡፡

 

በክልሉ ያለውን የቱሪዝም ጸጋ የማስተዋወቅ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑ  አመላክተው፤ በክልሉ የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች መኖራቸውን ገልጸዋል።

 

አልዌሮ ወንዝና ሰውሰራሽ ግድብ፣ ባሮ ወንዝና ድልድይ፣ አጁመራ የውጭ ዜጎች መካነመቃብር፣ ታታ ሐይቅ፣ ቡሬይ ሐይቅ፣ ጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ፣ የመጀንግ ባዮስፌር ሪዘርቭ እንዲሁም የአምስቱ ብሔረሰብ ባህልና የአካባቢ አሰፋፈር በክልሉ ካሉ የቱሪስት መስህቦች መካከል እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል።

 

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.