Fana: At a Speed of Life!

ሳውዲ አረቢያ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ወታደራዊ ግጭቱን እንዲያቆሙ ጥሪ አቀረበች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳውዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፋይሰል ቢን ፋርሃን አል ሳኡድ በሱዳን ውስጥ የሚፋለሙ ወገኖች ሁሉንም አይነት ወታደራዊ ፍጥጫ በማቆም ሀገሪቱን ወደ መረጋጋት መመለስ የሚያስችል ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ከሱዳን ጦር ሃይሎች ጄኔራል ኮማንደር አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጋር ባለፈው ቅዳሜ የስልክ ውይይት የነበራቸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ÷ በሱዳን ያሉ ተፋላሚ ወገኖች መረጋጋትንና ብሄራዊ ጥቅማቸውን እንዲያስቀድሙ መግለጻቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
የሰብአዊ ድጋፍ ስራ፣ የሲቪሎች እና የእርዳታ ሰራተኞችን ደህንነት ለማረጋገጥ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
በፈረንጆቹ ሚያዚያ 15 በሱዳን ጦር ኃይሎች እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል የትጥቅ ግጭት መቀስቀሱ በሀገሪቱ ሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል።
በሱዳን ተፋላሚ ወገኖች መካከል ሰላም ለማስፈን የተለያየ ጥረት ሲደረግ መቆየቱም ተመላክቷል።
ነገር ግን በርካታ ስምምነቶች ላይ ቢደረስም እርስበርስ በመወነጃጀላቸው ስምምነቶቹ ሲጣሱ ቆይተዋል፡፡
በፈረንጆቹ ሐምሌ 27÷ የሱዳን ጦር ኃይሎች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ልዩነት በመፈጠሩ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጋር በጂዳ የነበረውን ድርድር ማቆሙን ዘገባው አስታውሷል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.