የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸው ተገለጸ፡፡
ወደ ብሪክስ የኢኮኖሚ ቡድን ለመግባት ዝግጁ የሆኑት ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ቦሊቪያ እንደተካተተች የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮሄልዮ ማይታ ተናግረዋል።
በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከፈረንጆቹ ነሐሴ 22 እስከ 24 ቀን 2023 በሚካሄደው የብሪክስ ሀገሮች ጉባኤ ላይ የቦሊቪያ ፕሬዚዳንት ሉዊስ አርሴ እንደሚካፈሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልፀዋል፡፡
በስብሰባው ላይም ስለ ሀገራቸው የወደፊት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ያላቸውን ዕቅድ ያቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል፡፡
በፈረንጆቹ ሰኔ 12 ቀን 2023 ፕሬዚዳንት አርሴ ቦሊቪያ ቡድኑን ለመቀላቀል ያላትን ፍላጎት በይፋ ማሳወቃቸውንም ማይታ አንስተዋል፡፡
ሀገራቸው ወደ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ልማት ለማምራት እና ታዳጊ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደምትፈልግም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ቦሊቪያ ከአምስቱም የብሪክስ አባል ሀገራት ጋር መወያየቷን የገለፁት ሚኒስትሩ÷ ሂደቱ ረጅም ቢሆንም ሀገሪቱ በትክክለኛው መንገድ ላይ እንደሆነች እና ጠንክራ እየሰራች እንደምትገኝም ገልጸዋል፡፡
በሰኔ ወር ላይ የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ሪያብኮቭ ወደ 20 የሚጠጉ ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ፍቃደኞች ናቸው ሲሉ መግለፃቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት አርጄንቲና፣ ኢራን እና አልጄሪያ ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎታቸውን በመግለጽ ያመለከቱ ሀገሮች ሲሆን በዚህ ዓመት ደግሞ ሌሎች ሀገሮች ህብረቱን የመቀላቀል ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።
በጆሀንስበርግ በሚካሄደው ጉባኤ ብሪክስ ተጨማሪ አምስት ሀገሮችን በአባልነት ሊቀበል እንደሚችልም ዘገባው ጠቁሟል።
ብሪክስ የተባለው የኢኮኖሚ ህብረት ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን በአባልነት የያዘ መሆኑ ይታወቃል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!