የመደመር ጽንሰ ሃሳብ የህብረ ብሔራዊ አንድነት መሰረት ነው – አቶ አዲሱ አረጋ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመደመር ጽንሰ ሃሳብ የህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማስቀጠል መሰረት መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ ተናገሩ።
“መደመር ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ኢዜአ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት አቶ አዲሱ አረጋ እንዳሉት÷ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ባህል ለማዳበር የልዩነት ኃሳቦች የሚንሸራሸሩበት የውይይትና የምክክር መድረኮችን ማስፋት አስፈላጊ ነው።
የመደመር ጽንሰ ሃሳብ ኢትዮጵያ ችግሮቿን የምትፈታበትን መፍትሄ አመላካች ሃሳቦችን የወለደ ሀገር በቀለ እሴት መሆኑን ተናግረዋል።
ጽንሰ ሃሳቡ የታሪክ ጠባሳ የሆኑና የርዕዮተ ዓለም ግትርነት ለወለዳቸው እንቅፋቶች መፍትሔ መስጠት የሚያስችል እሳቤ ነው ብለዋል።
በመጠላለፍና በልዩነት ትርክት ላይ የተገነባው የፖለቲካ ባህል ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ጠቅሰው፤ የመደመር ጽንሰ ሃሳብ አብሮነትና መደጋገፍን በማጎልበት ህብረ ብሄራዊ አብሮነት ለማስቀጠል መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት መጎልበትና ለመደመር እሳቤ ሳንካ እየሆነ መምጣቱንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ሆኖ የቆየው “እኔ ያልኩት ካልሆነ” ጽንፍ አካሄድ ለሀገር ህልውና የማይበጅ በመሆኑ በመደመር መርህ መጓዝ ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡