የመዲናዋ የ2015 ዕቅድ አፈፃፀም እየተገመገመ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2015 የልማት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የ2016 በጀት ዓመት የልማት ዕቅዶች ላይም ውይይት ይካሄዳል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ድክመትና ጥንካሬዎችን በመለየት ለ2016 በጀት ዓመት ትምህርት ይወሰዳል ብለዋል።
የከተማችንን ነዋሪዎች ኑሮ ለማሻሻል ይበልጥ የምንዘጋጅበት መድረክ ይሆናል ያሉት ከንቲባዋ፤ በአንድ በጀት ዓመት ብቻ ከ12 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በመንግስት ከ5 ሺህ በላይ፤ በህብረተሰብ ተሳትፎ ከ7 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች እንደተጠናቀቁ አመልክተዋል።
በተግዳሮቶች ሳንሸነፍ የህዝባችንን የኑሮ ሸክም እያቀለልን በአዲስ የስራ ባህል ታላላቅ ፕሮጀክቶቻችንን እያጠናቀቅን ከተማችንን ለኑሮና ለስራ ምቹ ለማድረግ ይበልጥ በትጋት የተሰራበት ዓመት ነው ብለዋል።
ስኬቶቻችን የምንረካባቸው ሳይሆኑ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ማምጣት የሚያስችሉ ጠንካራ አመራርና ተቋም ለመገንባት መሰረት የምንጥልባቸው ይሆናሉ በማለት ገልጸዋል።
ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ፣ የውሸት ሪፖርትን ፣ ህዝብን ሆን ብሎ ማንገላታትን እና የመሳሰሉ ችግሮችን በመቅረፍ ተቋማዊ ስርዓት በመገንባት ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ቁመና ለመድረስ አመራሩ እንደሚጠናከርም ተናግረዋል።