በሀገር አቀፍ ደረጃ 12 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመኸር ሰብል ተሸፈነ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን ባለው ሂደት 12 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመኸር ሰብል መሸፈኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለፁ።
በ2016 በጀት ዓመት ከግብርና ግብዓት ስርጭት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለመቅረፍ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እና የ2016 ዓ.ም በጀት ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የእርሻና ሆልቲካልቸር፣ የእንስሳት እና ዓሳ ኃብት እንዲሁም የተፈጥሮ ኃብት ልማት ዘርፎች ላይ የአፈጻጸም ሪፖርትና የቀጣይ እቅድ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።
በመድረኩም የግብርና ሚኒስቴር፣ የክልል ግብርና ቢሮ፣ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አመራሮች እንዲሁም የሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ በ2015 በጀት ዓመት በዋና ዋና የግብርና ልማት ስራዎች ላይ ውጤታማ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ፥ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በእንስሳት እና አሳ ሃብት ልማት ላይ የተሻለ ስራ መከናወኑን ገልጸው ፥ በሌማት ትሩፋት ላይ ጥሩ ጅማሮ ታይቷል ነው ያሉት፡፡
የስንዴ ምርትን ከውጭ ማስገባት ሙሉ በሙሉ ከማቆም ባሻገር ለውጭ ገበያ ማቅረብ የተጀመረበት ዓመት እንደነበርም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በግብርናው ዘርፍ ላይ የተመዘገበው ውጤት በሌሎች ዘርፎች ላይ መነቃቃት የፈጠረ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ሆኖም በ2015 በጀት ዓመት አሲዳማ አፈር በማከም ረገድ ግን በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተሰራ ጠቁመዋል፡፡
በግብርና ግብዓት አቅርቦት ላይ ችግሮች መስተዋላቸውን ያነሱት የግብርና ሚኒስትሩ ፥ ዋና ምክንያቱም የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና ህገወጥነት መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
በበጀት ዓመቱ በዘርፉ ለታየው ስኬት የግብርና ባለሙያዎች፣ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል።
የ2016 በጀት ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በእንስሳት እና አሳ ሃብት ልማት እና የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብርን ማጠናከር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በግብርና ግብዓት አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም እንዲሁ፡፡
ለዚህ ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ ግዥን ቀደም ብሎ ከማከናወን ባለፈ ስርጭቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለመቆጣጠር እንደሚሰራ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በ2016 መኸር ወቅት 17 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ፥ እስካሁን ባለው ሂደት 12 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል ነው ያሉት፡፡